በሰሜን ኢትዮጵያ ለተራዘመው ጦርነት የአሜሪካ እና የምዕራባውያኑ ተጠያቂነት

276

መስከረም 03 ቀን 2015 (ኢዜአ) አሸባሪው ሕወሓት በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት በማድረስ በተላላኪነት ኢትዮጵያን ለመበተን ለሚሹ ሀይሎች መንገድ ከፋች ሆኖ ያስቀጠለው ጦርነት በትግራይ ክልል ተጀምሮ ወደ አጎራባች ክልሎች ተስፋፍቶ እንደነበር አይዘነጋም።

የሽብር ቡድኑ የለኮሰው ጥፋት የኢትዮጵያን ሰላም ካወከ ድፍን ሁለት አመታትን ሊያስቆጥር የአንድ ወር እድሜ ብቻ ቀርቶታል።

አሸባሪው ህወሓት በግፍና በወረራ ባስቀጠለው ጦርነት ሳቢያ የበርካታ ንጹሃን ዜጎች ህይወት አልፏል፣ በአማራና አፋር ክልሎች የሚገኙ ህዝቦችን ጨምሮ ከሶስት ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፣ የህዝብ ሀብት የሀገር ንብረት የሆኑ መሰረተ ልማቶች ወድመዋል።

ጦርነቱ ከጀመረበት ግዜ አንስቶ አሁን የደረሰበት ደረጃ እስኪደርስ ድረስ አሜሪካ እና አጋሮቿ የሆኑ ምዕራባውያን ጎራ ለይተው ለአሸባሪው ሕወሃት ድጋፍ የመስጠት አዝማሚያቸው በግልጽ ሲታይ መቆየቱን ‘ጌትፋክት’ የተሰኘ የዜና ምንጭ ስለ ሰሜኑ የጦርነት ሂደት ባሰፈረው ጹሁፉ አስነብቧል።

የቀድሞው የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ በቲውተር ገጻቸው አሸባሪው ሕወሓት ኢትዮጵያ ላይ የከፈተውን ጦርነት እንዲያቆም ተደጋጋሚ ጥሪ ቢያስተላልፉም ባይደን መራሹ የአሜሪካ መንግስት ግን ኢትዮጰያና ህዝቦቿን የሚጎዱና የሚያሸማቅቁ በቀጥታም በኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠሩ ኢፍትሃዊ መግለጫዎችን መስጠቱን ቀጥሏል።

በሌላ በኩል በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ፣ የጸጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያ ላይ ማእቀብ እንዲጥል በዝግ ስብሰባ ሲያነሳሱ መቆየታቸወን የተባበሩት መንግስታት የቀድሞው የስደት ጉዳዮች ሃላፊ ሞሪን አቺ ማጋለጣቸው ይታወሳል።

የጸጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያ ላይ ማእቀብ እንዲጥል የተደረገው ዘመቻ የአለም የጤና ድርጅት ዳይሬክተር እና የአሸባሪው ሕወሃት ቁንጮ አመራር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም እንዲሁም ሌሎች የአሸባሪ ቡድኑ ተባባሪዎች የተቀነባበረ ሴራም ነበር።

የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ እንዲጥል የባይደን አስተዳደር ጫና ቢያደርግም ምክር ቤቱ ከአምስት ግዜ በላይ ተሰብስቦ ካለ ስምምነት ተበትኗል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት፣ የአሜሪካ የተራድኦ ድርጅት እና ሌሎች የምዕራባዊያን ድርጅቶች የኢኮኖሚ ማዕቀብ እንዲሁም ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትን በግልጽ በማሳየት በኢትዮጵያ ላይ ጫና ሲፈጥሩ ቆይተዋል።

በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ የአሸባሪ ቡድኑ ሲመቸው ወጣቶች እና ህጻናትን ለጦርነት እያሰለጠነ፣ በአማራና አፋር ክልሎች ጦር እየሰበቀ፤ ሳይመቸው ሲቀር ደግሞ የኢትዮጵያን መንግስት እየከሰሰ አሳልፏል።

ቡድኑ ህጻናትን በጦርነት ለማሰለፍ ሲመለምልና ሲያሰለጥን፣ ለትግራይ ክልል ህዝብ በኢትዮጵያ መንግስትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሲቀርብ የነበረን የእርዳታ ቁሳቁስ ለጦርነት አላማ ሲያውልና አጎራባች ክልሎች ላይ እጅግ ዘግናኝ ጦርነት ሲከፍት ዝምታን የመረጡት አሜሪካ እና ምዕራባውያኑ፣ ይህን ግፍ የመከላከል ኃላፊነት ያለበት መንግስትና የየአካባቢው ህዝብ ራሱን ከሽብር ቡድኑ የመከላከል እርምጃ ሲወስድና ሕወሓት ተጠቃሁ ሲል እጅግ አሳፋሪ በሆነ መልኩ ዘብ ለመቆም ሲሯሯጡ በአደባባይ ታይተዋል።

ካልተገባ ጣልቃ ገብነት በመታቀብ ጦርነቱን ለማስቆም ትልቅ ድርሻ የነበራቸው አሜሪካ እና ምዕራባዊያኑ የተዛነፈ አቋም አንጸባርቀዋል፤ ለአብነትም መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም ባደረገበት ወቅት ሕወሃት ተመሳሳይ ርምጃ እንዲወስድ ግፊት ከማድረግ ይልቅ ዝምታን መርጠው ነበር።

በተጨማሪም መንግስት የሰብዓዊ እርዳታን ለትግራይ ክልል ለማድረስ የተኩስ አቁም ባደረገበት ወቅትም ምዕራባውያኑ ከሕወሓት አመራሮች ጋር ያልተገባ ግንኙነት ሲፈጥሩ ታይተዋል።

በመጨረሻም መንግስት የሰላም አማራጭን ለመተግበር ግልፅ እንቅስቃሴ በማድረግና ወደ ስራ በመግባት ላይ ባለበት ወቅት አሸባሪ ቡድኑ የሶስተኛ ዙር ጦርነቱን በአጎራባች ክልሎች ላይ ሲከፍት አሁንም እንደለመዱት ዝምታን መርጠዋል።

አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት ሕወሓትን በመደገፍ ኢትዮጵያን ወደ ማያባራ ጦርነት እየመሯት ሲሆን በጦርነቱ ሳቢያ የሞቱ ንጹሃን እና የተፈናቀሉ ዜጎች የአሸባሪ ቡድኑ ሃላፊነት ብቻ ሳይሆን ይልቁኑም ቡድኑን ደግፈው ለዚህ ያበቁት አሜሪካ እና አንዳንድ ምዕራባዊያን ሃላፊነት ጭምር ነው።

የባይደን አስተዳደር እና ምዕራባዊያኑ በአሸባሪው ቡድን ጭካኔዎች ላይ ዝምታን ከቀጠሉ እና በዴሞክራሲያዊ መንገድ በህዝብ ድምጽ የተመረጠውን የኢትዮጵያ መንግስት ካልደገፉ አሁንም ጦርነቱ ማብቂያ ወደሌለው ምዕራፍ መሸጋገሩ አይቀርም ሲል ጌትፋክት ጽሁፉን አጠቃሏል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም