በትግራይ በአዲሱ የትምህር ዘመን ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቷል

61
ማጭጨው/ሁመራ መስከረም 9/2011 በመማር ማስተማር ሒደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታትና ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ የድርሻቸውን እንደሚወጡ የትግራይ ምዕራባዊና ደቡባዊ ዞኖች መምህራን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ገለጹ። በክልሉ ደቡባዊ ዞን እምባ አለጀ ወረዳ የእልባት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህር ዙፋን በላይ እንደገለጹት በያዝነው የትምህርት ዘመን ለትምህርት ጥራት ቀዳሚ ትኩረት ተሰጥቶቷል። “ካሁን በፊት መምህራን ከሰለጠኑበት ሙያ ውጪ በመመደብ በትምህርቱ ጥራት ላይ ችግር ሲያጋጥም መኖሩን ጠቅሰው ዘንድሮ የዚህ አይነት ምደባ አይኖርም” ብለዋል፡፡ ለቀጣይ የትምህርት ደረጃ ብቃት ያላቸውና የሌላቸው ተማሪዎችን በጅምላ በማሳለፍ ይደረግ የነበረውን እንቅስቃሴ እንደሚቀር የተናገሩት ደግሞ በወረዳው የመለስ መሰናዶ ትምህርት ቤት ርእሰ-መምህር ደጀን ይሀልው ናቸው፡፡ የተማሪዎች  ስነ-ምግባር ያልጠበቀ በቡድን የመኮረጅ እንቅስቀሴን  በማረም የተሻለ የመማር ማስተማር ሂደት ለማረጋገጥ እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡ የትምህርት ጥራት ለመረጋገጥ ፣የወላጆች ተከታታይ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ በክልሉ ምእራባዊ ዞን የዓዲጎሹ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ምግላ ብፈረስ ትምህርት ቤት መምህር አማሃ ክፍሉ ናቸው። ወላጆች በትምህርት ቤት ያላቸውን ተሳትፎ ከፍ በማድረግ ለተሻለ ውጤት መረጋገጥ በጋራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል። የቃፍታ ሑመራ ትምህርት ጽህፈት ቤት ምክትል አስተባባሪ መምህር አዲስአለም  ኪዱ  በበኩላቸው በወረዳው ከትምህርት ጥራት ችግር በተጨማሪ ትምህርት የሚያቋርጡ የተማሪዎች ቁጥር ከፍ ያለ መሆኑን ገልጸዋል። በያዝነው የትምህርት ዘመን እነዚሁ የተለዩ ችግሮችን በመቅረፍ የተሻለ ተወዳዳሪ ተማሪ ለመፍጠር ትኩረት እንደሚሰጡ ገልጸዋል፡፡ የትምህርት ጥራትን ከማረጋገጥ በተጨማሪ ትምህርት ለሚያቋርጡ ተማሪዎች ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅት መደረጉን የተናገሩት ደግሞ የምእራባዊ ዞን ትምህርት አስተባባሪ አቶ ዳንኤል መሰለ ናቸው። ባለፈው የትምህርት ዘመን በትምህርት ገበታ ከነበሩ ከ147 ሺህ በላይ ተማሪዎች ውስጥ ከ3ሺህ በላይ ተማሪዎች ትምህርት ማቋረጣቸውን ገልጸዋል። ችግሩን ለመፍታት ከወላጆችና ከተማሪዎች ጋር በመወያየት ለመስራት የሚያስችል መርሀ-ግብር መዘጋጀቱንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም