ለዘመናት ህዝቦችን ያስተሳሰረውን ገመድ አሸባሪው ህወሓት በእብሪት ተነሳስቶ ለመበጠስ እየሰራ ነው

169

ባህር ዳር፣ ጳጉሜን 3 /2014(ኢዜአ) ለዘመናት ህዝቦችን አስተሳስሮ የቆየውን የግንኙነት ገመድ አሸባሪው ህወሓት በእብሪት ተነሳስቶ ጦርነት በመክፈት ለመበጠስ እየሰራ ነው ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ገለጹ።

የመከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ጦርነቱን በመመከት እያደረጉት ያለው ተጋድሎ ኢትዮጵያ በደምና አጥንታቸው ሉአላዊነቷን የሚያስከብሩ ልጆች ዛሬም እንዳሏት ማሳያ ነው ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ዶክተር ይልቃል ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፣ አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ዓልሞ ለ3ኛ ጊዜ ጦርነትና ወረራ ከፍቷል።መንግስት ጦርነት ለማካሄድ ፍላጎትም ሆነ በጦርነት የሚገኝ መፍትሄ እንደሌለ ስለሚያምን የሰላም አማራጭ በማቅረብ የሚችለውን ርቀት መሄዱን ገልጸዋል።

"መንግስት ለሰላም ካለው ጽኑ ፍላጎት ኮሚቴ በማዋቀር፣ አጀንዳዎችን በመለየትና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለሰላም ፍላጎቱን ቢያሳይም እብሪተኛው ህወሓት ዛሬም ሰላምን ወደጎን ብሎ ፍላጎቱን ለማሳካት ጦርነትን ብቸኛ አማራጭ አድርጓል" ብለዋል ዶክተር ይልቃል።

በከፈተው ጦርነት ኢትዮጵያን ለውጭ ጠላት አሳልፎ ለመስጠት መነሳቱ ሳይበቃ በአዋሳኝ አካባቢ የሚገኙ የአማራና የአፋር ህዝቦች ላይ ግድያ፣ የአካል ማጉደል እንዲሁም የንብረት ዘረፋና ውድመት እየፈጸመ መሆኑን አስረድተዋል።

"በእዚህም የሽብር ቡድኑ ዳግመኛ ታሪክ ይቅር የማይለው በደል በህዝብ ላይ ማድረሱን ቀጥሎበታል" ያሉት ዶክተር ይልቃል፣ በእብሪተኝነትና በደመኝነት ተነሳስቶ የህዝቦችን የቆየ አብሮነት ለመበጠስና ግንኙነታቸውን ለማሻከር ቆርጦ መነሳቱንም ተናግረዋል።

"የትግራይ ህዝብ ከአማራ ህዝብ ጋር አብሮ የመኖር፣ የመስራት፣ የማደግ ህልምና ፍላጎት ያለው መሆኑን የአማራ ክልል መንግስትና ህዝብ በፅኑ ያምናል" ሲሉም ርዕሰ መስተዳደሩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የጸጥታ አካላት ለሀገርና ለህዝብ ህልውና እየከፈሉት ባለው መስዋዕትነት የነጻነትና ሉአላዊነት ጠንካራ ማሳያ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

የወገን ጦር አባላት የሽብር ቡድኑን በመመከት እያደረጉት ያለው የጀግንነት ተጋድሎ ኢትዮጵያ በደምና አጥንታቸው ሉአላዊነቷን የሚያስከብሩ ልጆች ዛሬም እንዳሏት ማሳያ ነው ሲሉም ዶክተር ይልቃል ተናግረዋል።

ዶክተር ይልቃል እንዳሉት አሸባሪው ህወሓት በተካነበት የሀሰት ትርክት ትውልዱን በጥላቻ ከመመረዝ ባለፈ በየደረሰበት ንጹሀንን እየገደለ፣ እያቆሰለ፣ እያፈናቀለና ሃብትና ንብረት እየዘረፈ ይገኛል።

"አሸባሪው ህወሓት በደልና ግፍ አሜን ብሎ የሚኖር ህዝብ እንደሌለ ጠንቅቆ ሊያውቀው ይገባል'' ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ መላው ኢትዮጵያዊ ለነጻነቱ፣ ለህልውናው፣ ለክብሩና ለአገር አንድነት ቁርጠኝነቱን እያሳየ መሆኑንም ገልጸዋል።

ለእዚህም የአማራ ክልል ህዝብን ጨምሮ መላ ኢትዮጵያዊያን በስንቅ፣ በደም ልገሳና በተለያየ መንገድ ሠራዊቱን በደጀንነት በማገዝ እያሳዩት ያለው ቁርጠኝነት የኢትዮጵያን አንድነት ለማስቀጠል የቆረጠ ህዝብ እንዳለን ማረጋገጫ ነው ሲሉ ዶክተር ይልቃል ገልጸዋል።

የህወሓትን ወረራ ለመመከት በግንባር እየደረገ ላለው ትግል ህዝቡ በደጀንነት የሚጠበቅበትን ለመወጣት እያደረገ ያለውን ጥረት እንዲያስቀጥልም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም