የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት የፍጆታ ዕቃዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ ህብረተሰብ አቀረበ

168

አዲስ አበባ ጳጉሜን 2/2014 (ኢዜአ) የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት አዲስ ዓመትን በማስመልከት መሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችን በበቂና በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ ህብረተሰብ ማቅረቡን አስታወቀ።

ድርጅቱ በአገሪቱ ከ80 በላይ ቅርንጫፎቹ ለኢንዱስትሪ ግብዓት ከሚሆኑ ምርቶች ባለፈ መሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችን ለህብረተሰቡ እያቀረበ መሆኑም ታውቋል።

ለአዲስ ዓመት ከ15 ሚሊዮን ሊትር በላይ የምግብ ዘይት፣ ከ10 ሺህ 500 ኩንታል በላይ ዱቄትና ሌሎች የፍጆታ ዕቃዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረቡን ገልጸዋል።

የድርጅቱ የግዢ ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰሎሞን ግርሻ፤ በዓልን አስመልክቶ የፍጆታ ዕቃዎች እጥረት እንዳይፈጠር ሰፊ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

በተለይ እጥረት በሚፈጠርባቸው የምግብ የዘይት፣ የዱቄትና ሌሎች መሰረታዊና መደበኛ የሚባሉ የፍጆታ ዕቃዎች በበቂና በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ ቀርበዋል ብለዋል።

ለህብረተሰቡ በቂ የኢንዱስትሪ ምርቶችንና የፍጆታ እቃዎችን የማቅረብ አደረጃጃትና አቅም መፈጠሩን ጠቅሰው ለበአል የሚሆኑ ምርቶችን በብዛትና የህብረተሰቡን የኑሮ ደረጃ በማካለ ዋጋ እንዲቀርብ ተደርጓል ብለዋል።

ህብረተሰቡ ለበዓል በቂ የሆነ የፍጆታ ዕቃ መቅረቡን ተገንዝቦ ምርት በመደበቅ እጥረት በሚፈጥሩ ህገ-ወጦች ሊደናገር እነደማይገባ ተናግረዋል።

ድርጅቱ ባለ ሶስት ሊትር ዘይት 380 ብር፣ ባለ አምስት ሊትር 635 ብር በሁሉም ቅርንጫፎቹ እያከፋፈለ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

ዘይትን ጨምሮ ሌሎች ሸቀጦችም በበቂ ሁኔታ በመቅረባቸው ምንም አይነት የዋጋ ጭማሪና የምርት እጥረት እንደማይኖርም ተናግረዋል።

የሸማቾችን ፍላጎትና አቅርቦት ለማመጣጠን መንግስት ስፊ ጥረት እያደረገ በመሆኑ በዚህም የሚታዩ ለውጦች ተመዝግበዋል ነው ያሉት።

ከበዓል በኋላ ወደ አገር ውስጥ የሚገባ 20 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ከውጭ ለማስገባት ድርጀቱ ውል መፈጸሙን የጠቆሙት አቶ ሰሎሞን የፓስታ መኮሮኒ፣ የሩዝና መስል የፍጆታ እቃዎች በብዛት ማስገባቱን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም