ደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ነገ ይመረቃል

4216

ደምቢዶሎ ግንቦት 11/2010 በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን ደምቢ ዶሎ ከተማ የተቋቋመው ደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ነገ እንደሚመረቅ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት አስታወቁ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ደለሳ ቡልቻ ለኢዜአ እንዳሉት ከአራቱ የግንባታ ምዕራፎች አንደኛው ተጠናቆ በ35 የትምህርት ክፍሎች 1 ሺህ 500 ተማሪዎችን ማስተማር ጀምሯል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ትውልድን ለመቅረጽ፣ ለምርምርና ለህብረተሰብ አገልግሎት በተለዬ መልኩ እየሰራ እንደሚገኝም ነው ፕሬዝዳንቱ ያብራሩት፡፡

በሌሎች የሀገሪቱ ዩኒቨርስቲዎች የሌለ የኢንተርፕርነርሺፕና ስራ ፈጠራ የትምህርት ክፍል መቋቋሙን ገልጸው ይህም ለሀገሪቱ ህዳሴ  የድርሻውን እንደሚያበረክት ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በምርምር ስራው ላይ በተለይ የአካባቢውን የተፈጥሮ ሃብት መሰረት አድርጎ ለመስራት መዘጋጀቱንም ዶክተር ደለሳ አረጋግጠዋል፡፡

በሀገሪቱ ከተቋቋሙ 11 አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ የሆነው ደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች መገልገያዎችና አስፈላጊ የትምህርት ግብዓቶች ከስር ከስር እየተሟሉለት መሆኑንም ፕሬዝዳንቱ  ተናግረዋል፡፡

በ2008 የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት ይኼው ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያው የግንባታ ምዕራፍ  በአንድ ዓመት ጊዜ ተጠናቆ ነው ለአገልግሎት የበቃው፡፡

በምርቃት ስነ ስርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድን ጨምሮ የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳና ሌሎች የፌደራልና የክልል መንግሥታት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡