ግጭትም መልክ አለው!

87
ሠይፌ  ደርቤ /ኢዜአ/:-  በየጊዜው የነበሩ እና ያሉ የኢትዮጵያ መንግስት ህጎች ለአገር ልማድና ባህላዊ ህጎች፣ በህጎቹም ለሚፈፀሙ የእርቅ ጉዳዮች እውቅና ይሰጣሉ። ለምሳሌ የኢፌዴሪ ህገ መንግስት በአንቀፅ 34 ንዑስ አንቀፅ 5፣ ህገመንግስቱ በባህላዊ ህጎች መሰረት መዳኘትን እንደማይከለክል ያስረዳል። በ1952 ዓ.ም የወጣው የኢትዮጵያ የፍትሀ ብሄር ህግና በ1959 የወጣው የፍትሀ ብሄር ህግ ስነ ስርዓት ግልግልን ወይም እርቅን ወዘተ... የግልግል ወይም የቤተዘመድ ሽምግልና ዳኝነት ብይን በፍርድ ቤት እንደሚሰጥ የፍርድ ውሳኔ አይነት ተዘጋጅቶ የካሳንና የኪሳራን ጉዳይ ለመወሰን እንደሚችል (በፍትሀ ብሄር ስነ ስርዓት ህግ ቁጥር 318 /2/) ይገልጻል። በተለይ ባህላዊ ህጎቹ ማህበረሰቡ በአካባቢው ልማድና ባህል መሰረት ፈቅዶና ተስማምቶ ሊዳኝባቸው እንደሚችልም ያስረዳሉ። ይህም ሆኖ በተለያዩ ጊዜያት ግጭቶች በሚነሱባቸው አካባቢዎች ያሉ የአስተዳደር አካላትም ሆኑ የክልል መንግስታት በባህላዊ ተቋማቱ ሲጠቀሙና ግጭቶችን ሲፈቱ እምብዛም አይስተዋልም። ሆኖም ባህላዊ ተቋማቱ የሚፈቱት ግጭትና የሚያደርጉት እርቅ በበቂ ስምምነትና መግባባት ላይ ስለሚመሰረት፣ ሽማግሌዎችም ስለሚከበሩ፣ እርቅን ማፍረስ ከነውርም የባሰ ነውር ተደርጎም ስለሚቆጠር እርቆቹ የፀኑ ሆነው የሚኖሩበት እድል ከፍተኛ ነው። በአገራችን በሁሉም ክልሎችና ጎሳዎች፣ ብሄሮች ወዘተ... ግጭቶች ሲያጋጥሙ መፍትሄ መስጠት የሚችሉ በርካታ ባህላዊ ተቋማትና ሽማግሌዎች እያሉ፣ መንግስትን ብቻ እየጠበቁና መንግስት ይህን ያድርግ እያሉ መጓዙ ብቻውን ተገቢ አይሆንም። ዘላቂ ሰላም ለማምጣትና ችግሩ እንዳይደገም ለማድረግ ለባህላዊ የግጭት መፍቻ ተቋማትና ለሽማግሌዎች ወይም ሸንጎ አስተዳደር ልዩ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል። በነገራችን ላይ ግጭት በሰው ልጆች የዕለት ተዕለት ህይወትና መስተጋብር ምክንያት ሊፈጠር የሚችል፣ በአግባቡ ከተያዘም ለእድገትና ለሰው ልጆች ፍላጎት መሟላት ምክንያትና ጤናማ ጎኑ ከፍ ያለ መሆኑን በግጭት መንስኤና አፈታት ዙሪያ ጥናት ያደረጉ በርካታ የዘርፉ ምሁራን ይገልፃሉ። የግጭት አፈጣጠርን በሚመለከትም ምሁራኑ መንስኤ ብለው የሚጠቅሱአቸው በአብዛኛው እነዚህን አራት ጉዳዮች ነው። 1ኛ/ ግጭት፣ የሰው ልጆች ዓላማና ግብ ተኮር እንዲሁም ምክንያታዊ በመሆናቸው ግባቸውን ማሳካት ሳይችሉ ሲቀሩ በፍላጎቶቻቸው እውንነት ላይ ተስፋ ቆርጠው ወደ ብጥብጥና ግጭት ይገባሉ ይላሉ። 2ኛ/ የሰው ልጆች የተሻለ ህይወትና ኑሮ ለማግኘት ያስችለናል ብለው የጠበቁት ጉዳይ ሳይሳካ በመቅረቱ ምክንያት ለጉዳዩ አስቀድሞ የነበራቸው መተማመን በተጨባጭ ከተገኘው ውጤት ጋር ሲመዘን በሚደርስ አለመጣጣም ክፍተት ይፈጥርባቸዋል፤ ያሰቡትና የሆነው እውነት መለያየትም ለግጭትና ብጥብጥ ይዳርጋቸዋል ይላሉ። 3ኛ/ ግጭት እንዲነሳ ሁለት ቡድኖች ለአንድ ግብ መሳካት ወይም ተጨባጭ እውነታ ተፈፃሚነት የእኔ ነው ትክክል ብለው የሚያቀርቡት እርስ በእርስ የማይጣጣም ወይም የተለያየ አስተሳሰብ የግድ መኖር አለበት ይላሉ። ይህ ሁኔታ ወደ አለመግባባት በመውሰድ አንዱን በሌላው ላይ ጥገኛ እንዲሆን እንደሚያደርገውም ይገልጻሉ። በሌላ አነጋገር በሁለት ወገኖች በሚፈለግ አንድ ጉዳይ ወይም አንድ ነገር ላይ ያለ የጥገኝነት ስሜት የሚፈጥረው ጤናማ ያልሆነ ውድድር የግጭት መንስኤ ይሆናል ይላሉ። 4ኛ/ ስር የሰደደ ግጭት የሚፈጠረው የሰው ልጆች መሰረታዊ ፍላጎታቸውን ማሟላት አንችልም፣ ምንም ነገርም ሊሳካልን አይችልም የሚል ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሲገቡ ነው ይላሉ። በእነዚህ ፍላጎቶች አለመሟላት የሰው ልጆች ለግጭት ሊዳረጉ ይችላሉ ሲሉ ይገልፃሉ።   ወደ አገራችን ሁኔታ ስንመጣ፣ በአገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታዩ ያሉ ግጭቶች በእነዚህ አራት ምክንያቶች የማይካተቱ ናቸው። የግጭቶቹ ሁኔታዎችም ሆኑ የሚደርሱት ጥፋቶች ተፈጥሯዊ መልክና ገፅታ የላቸውም። ሰው ሰራሽ ናቸው የሚባሉትም ለዚሁ ነው። ግጭቶቹና በግጭቶቹ በሚከሰቱ ጥፋቶች ተዋናይ በመሆን አውቀውም ይሁን ሳያውቁ የሚሳተፉ ወገኖች ዓላማ የላቸውም። በአገራችን ከተፈጠረው አዲስ ጭላንጭልና የተስፋ ብርሃን አኳያም ሰዎች ግጭቶቹን እንዲያነሱ የሚገፋፋቸው የተስፋ መቁረጥ አመክንዮም የለም። በግጭቶቹ ጎጂና ተጎጂ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በፀብና ብጥብጡ ሊያሳኩት የሚፈልጉት ዓላማም የለም። በጉርብትናም ሆነ ተሰባጥረው ሲኖሩ በነበሩት ህዝቦች መካከል ከመሰረታዊ ፍላጎት ጋር የተያያዘ አዲስ ፍላጎትን በማጣት መልክ የሚከሰት የግጭት መንስኤም የለም። ይልቁንም አዲስ ብርሃናማ ተስፋ ተፈጥሯል፤ በዚህም ዙሪያ መላው ህዝብ ተግባብቷል። ልንጠፋ ከነበረበት ድነናል። የመከበብ ስጋታችን እየተቀረፈ ሄዶ፣ የተሻለ ጉርብትናና የተጠቃሚነት ትስስር መፈጠር ጀምሯል። ከስጋት ይልቅ፣ ተስፋ፣ ከጨለማ ይልቅ ብርሃን እየታየ ባለበት ሁኔታ ደስታችንና ተስፋችን ግጭትን ሳይሆን አብሮነትንና ትስስርን ሊያጠናክርልን ካልሆነ በቀር መገፋፋትንና መሳደድን አያመላክተንም። ከላይኞቹ የምሁራን አመክንዮ አኳያም የግጭት ብያኔዎቹ ከነባራዊ ሁኔታዎቻችን ጋር የማይጣጣሙ፣ የዜጎቻችን ያልሆኑ ይልቁንም ድንገቴዎች መሆናቸው በአገራችን እየታየ ያለውን አርቴፊሻል ወይም ይሁነኝ ተብሎ የተፈጠረ ግጭት መልከ ቢስ ያደርገዋል። በዚህም ምክንያት በአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች እየተከሰቱና ተከስተው የነበሩ ግጭቶች ተፈጥሯዊ መልክ ሊኖራቸው አይችልም። በእርግጥ ለዚህም ነው በሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ከወራት በኋላ ወደ ነበሩበት እየተመለሱ ያለው፤ መፈናቀሉ በደረሰባቸው አካባቢዎችም ተፈናቃዮቹ ወንድሞቹና እህቶቹ ወደነበሩበት እንዲመለሱለት የየአካባቢው ህዝብ እየጠየቀም እየተባበረም የሚገኘው። በመሆኑም ይሄ ህዝብን እርስ በእርስ በማበጣበጥ በዜጎች ህይወት መጥፋት ጊዜያዊ ትርፍ ለመግኘት የቋመጠና የሚቋምጥ ሃይል ርባና ቢስ ነው። ይልቁንም ባሳደረው ጠባሳና ዘግናኝ ተግባር በራሱ ላይ አጉል ታሪክ እየፃፈ ነው። በዚያው ልክ ይህ ሀይል ዜጎች በሞት እንዲቀጠፉ ቢያደርግም የብጥብጡ አቀናባሪም ሆነ ለኳሽ በመንፈስም፣ በሞራልም ከሳሪና ሙት ነው። ትልቁ ሞት ደግሞ ይሄ ነው። ይህን ሙት የሆነ በዜጎች ህይወት የሚቀልድ ሃይል በህግ መከላከሉና ተጠያቂ ማድረጉ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ዜጎች በየአካባቢያቸው ሰከን ብለው እንዲወያዩና እያንዳንዱን የብጥብጥ መንስኤና የግጭት አነሳስ እንዲመረምሩ በተለይ የየአካባቢው አስተዳደር ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይገባል። ይህ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠርም የፌዴራሉና የክልል መንግስታት ተገቢ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ጉዳዩ በህግ እንዲታይ ከማድረግ በተጓዳኝ፣ የችግሩን ማጠንጠኛ፣ የሴራውን ባለቤትና ተግባር መላው ህዝብ አውቆት ባሳደረው ጠባሳና አሳፋሪ ታሪክ እንዲመዘገብ፣ ትውልድም በቅብብሎሽ እንዲማርበት ማድረግ ይኖርባቸዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም