ከውጭ የሚገቡ የግብርና ምርቶችን በአገር ውስጥ የማምረት ዘዴን በማጠናከር የዋጋ ግሽበቱን ለመቀነስ መስራት ይገባል

238

ነሐሴ 28 ቀን 2014 (ኢዜአ) ከውጭ የሚገቡ የግብርና ምርቶችን በአገር ውስጥ የማምረት ዘዴን በማጠናከር የዋጋ ግሽበቱን ለመቀነስ መስራት እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበር ገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበር የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በሚመለከት ውይይት ያካሄደ ሲሆን በመድረኩም የማህበሩ አባላትና በዘርፉ የሚሰሩ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡

በመድረኩም ከአገር ውስጥ ችግሮች ባሻገር በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የጂኦ-ፖለቲካ መቀያየር በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ራሱን የቻለ ተጽእኖ እየፈጠረ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፕሮፌሰር መንግስቱ ከተማ እንዳሉት፤ የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ተጽእኖ ፈጥሯል፡፡

የሁለቱ አገራት ጦርነት በተለይ ለዋጋ ግሽበት መባባስ ምክንያት እየሆነ መምጣቱን ጠቅሰው፤ ችግሩን ለመከላከል የፖሊሲ ማሻሻያ እስከ ማድረግ የሚደርስ ውሳኔ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ሁለቱ አገራት ለዓለም ገበያ የሚያቀርቡትን ከፍተኛ የሆነ የግብርና ምርት በመቀነስ ላይ በመሆናቸው ከውጭ የሚገቡ የግብርና ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ነው ያሉት፡፡

የአፈር ማዳበሪያን በአገር ውስጥ ለማምረት ጥረት ማድረግ እንደሚገባና ነዳጅን ጨምሮ ሃብትን በቁጠባ መጠቀም ይገባል ነው ያሉት፡፡

በማህበሩ ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር አረጋ ሹመቴ በበኩላቸው፤ በሁለቱ አገራት ጦርነት በዋናነት በምግብ፣በነዳጅና በማደበሪያ ዋጋ ላይ ግሽበት እንዲፈጠር ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት  የዋጋ ግሽበቱ አንጻራዊ መሻሻል እያሳየ መሆኑን ጠቅሰው፤ የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያውን በተገቢው መልኩ ተግባራዊ በማድረግ ችግሩን በዘላቂነት መቅረፍ እንደሚገባም መክረዋል፡፡

በተለይ በግብርና እና ኢንዱስትሪ ዘርፎች ላይ ሰፊ ኢንቨስትመንትን ማስገባት፣ የዋጋ ግሽበት፣ስራ-አጥነት እና የውጭ ምንዛሬን እጥረትን መቅረፍ ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበር ገለልተኛ እና ለትርፍ ያልተቋቋመ ማህበር ሲሆን፤ በዋናነት  ከምጣኔ ሀብት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ ጥናት በማድረግ ለፖሊሲ አውጪዎች ምክረ-ሀሳብ ያቀርባል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም