በአካባቢ ጥበቃ እና በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ዙሪያ ጥናትና ምርምሮችን ማካሄድ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

145

ነሃሴ 27/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ከዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት ጋር በአካባቢ ጥበቃ እና በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ዙሪያ ጥናትና ምርምሮችን ማድረግ የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ እና የዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት የኢትዮጵያ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ገመዶ ዳሌ ጋር በጋራ መሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

በዚሁ ወቅት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ እንደገለፁት ኢኒስቲትዩቱ ለአካባቢ ጥበቃ እና አረንጓዴ ኢኮኖሚ ላይ የተለያዩ የምርምር ስራዎችን እያካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

አያይዘውም የዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት የኢትዮጵያ ቢሮ ጋር የተደረገው ስምምነት የተጀመረውን ስራ ያግዛል ብለዋል።

ስምምነቱ ለምርምር የሚረዱ መረጃዎችን ለማግኘትና ተቀናጅቶ ለመስራት እንዲሁም ለምርምር የሚያግዝ ሀብት ለማግኘት ይረዳል ብለዋል።

በተጨማሪም መሰል የጥናት ስራዎች ከፍተኛ ገንዘብ ስለሚፈልጉ ከገንዘብ ድጋፉ ባሻገር ኢኒስቲትዩቱ የምክር ድጋፍም ያገኛል ነው ያሉት።

በአካባቢ ጥበቃና በአረንጓዴ ኢኮኖሚ የሚሰሩ ምርምሮች መንግስት በሀገሪቱ ተግባራዊ ለሚያደርጋቸው ፖሊሲዎችም በግብዓትነት የሚያገለግሉ መሆኑን ጠቅሰዋል።

”መንግስት አንድ ፖሊሲ ከመቅረጹ በፊት በቂ እውቀት ያስፈልገዋል፤ መረጃ ያስፈልገዋል፤ አንድ አካባቢ ምንም አይነት እጽዋት መብቀል እንደሚችል በጥናት መረጋገጥ አለበት''።ብለዋል

ከዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት የኢትዮጵያ ቢሮ ሀላፊ ዶክተር ገመዶ ዳሌ በበኩላቸው ለሀገሪቱ ጠቃሚ የሚሆኑ ፖሊሲዎችን ለማውጣት የምርምር ስራ ከሚሰሩ ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ መስራት  ያስፈልገናል ሲሉ ተናግረዋል።

የተሻሉ ወደ ፊት የተራመዱ የፖሊሲ ሀሳቦችን ከሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ ለመቀመርና የሚታዩ ክፍተቶችን መለየት የሚያስችል ስራ በጋራ ይሰራል ብለዋል።

''ያደረግነው የስምምነት ፊርማም ኢኒስቲትዩቱ በሚሰራቸው ጥናቶች ላይ አስፈላጊውን ምክረ ሀሳብ ለማቅረብ እና ድጋፍ ለማድረግ ያግዛልም'' ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም