የዞኑ ወጣቶች አሸባሪዎቹን ህወሃትና ሸኔውን ለመደምሰስ ከመንግስት ጎን እንሰለፋለን---ወጣቶች

110

ፍቼ ነሃሴ 26/2014 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ከሰሜን ሸዋ ዞን የተውጣጡ ወጣቶች የኢትዮጵያን ሉአላዊነትና አንድነት ለማፍረስ የተነሳውን የህወሃት አሸባሪ ቡድንና አሸባሪ ሸኔን ለመደምሰስ ከመንግስት ጎን ተሰልፈው እንደሚታገሉ አስታወቁ፡፡

ከዞኑ13 ወረዳዎች የተውጣጡ ወጣት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ በፍቼ ከተማ ውይይት  ተደርጓል፡፡

ወጣቶቹ አሸባሪው ህወሃት ለሶስተኛ ጊዜ የከፈተው ጦርነት መንግስት ችግሮችን በሰላም ለመፍታት ያስቀመጠውን አማራጮች የሚያደናቅፍ በመሆኑ ከመንግስት ጎን ተሰልፈው ለሀገር አንድነትና ሉአላዊነት እንደሚታገሉ ባወጡት መግለጫ አመላክተዋል፡፡

ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ያላቸውን ደጀንነት አጠናክረው በመቀጠል የሽብር ቡድኑንና ተላላኪዎቹን በአጠረ ጊዜ ድል ለማድረግ ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል፡፡

ወጣቱ በተለያዩ መንገዶች የሚሰራጩ የሃሰት መረጃዎችን ከመቀበልና ከማስተጋባት በመቆጠብ ለሀገር በሚጠቅሙ ተግባራት ላይ እንደሚያተኩሩ አመልክተዋል፡፡

የዞኑ ወጣቶች ማህበር ሊቀመንበር ወጣት ሽመልስ ጣፋ በውይይቱ ላይ እንደገለፀው አሸባሪው ሕወሃትና ተላላኪው ሸኔ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች አፍራሽ ተልእኮ ለማስፈጸም እየሰሩ ነው ብሏል፡፡

ወጣቱ በተለያዩ የጥፋት አጀንዳዎች ሳይታለል ለሀገሩ ሉአላዊነትና አንድነት መጠናከር የሚጠይቀውን ታሪካዊ  ሃላፊነት ማበርከት እንዳለበት አስገንዝቧል፡፡

በተለይ አካባቢውን ከሰርጎ ገቦች መጠበቅ፣የሃሰተኛ መረጃ አሰራጮችንና ግብረ አበሮቻቸውን ማጋለጥ እንደሚገባው አስረድተዋል፡፡

ከተሳታፊዎቹ መካከል የሂደቡ አቦቴ ወረዳ ወጣት ሲርቦ ሙሃመድ አሸባሪው ህወሃት ለሰላም የተዘረጋለትን እጅ በመግፋት እድሜያቸው ያልደረሱ ታዳጊዎችን በጦርነት እንዲማገዱ፣ ንብረት  እንዲወድም ማድረጉ የሚወገዝ ተግባርና ከተጠያቂነት የማያስቀር መሆኑን ተናግሯል፡፡

ሌላው አስተያየት ሰጪ ወጣት የሺ ቦንሳ እንዳለችው አሸባሪው ህወሃት ሀገርን የማፍረስና የቡድኑን መሪዎች ፍላጎቱ ለማሳካት የከፈተው ጦርነት እንጂ የትግራይ ሕዝብ ፈላጎት ያማከለ አይደለም፡፡

የቡድኑን ፍላጎት በማምከን የኢትዮጵያን አንድነት፣ ህብረትና ሉአላዊነት የሚያጠናክሩ ስራዎችን  ማከናወን ይጠበቅብናል ብላለች፡፡

በውይይቱ ላይ ከዞኑ የተለያዩ ማህበራትና አደረጃጀቶች የተውጣጡ 250 ወጣቶች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም