ለግማሽ ምእተ-ዓመት የዘለቀ የሽብር ትርክት

166

አሸባሪው ህወሃት ላለፉት 47 ዓመታት በይዘትም በቅርፅም ለውጥ ያላደረገበትና በንጹሀን የትግራይ ተወላጆች ደም በስልጣን ለመቆየት ያዘጋጀው፤የትግራይ ወጣቶችንም ለጦርነት የሚያነሳሳበት መዝሙር አለው።

የሽብር ቡድኑ “ዘይንድይቦ ጎቦ…” በሚለው መዝሙሩ፣ ደም አፋሳሽነት፣ ጥላቻ፣ ጦረኝነት፣ሰላም ጠልነትን፣ አልቦ እብሪተኝነትን ያውጅበታል።

በመዝሙሩም እንኳን ህሊናን አጥንትንም ዘልቀው የሚሰሙ ሰቅጣጭ የጥላቻ ተረኮች ታጭቀዋል።

በተለይም የትግራይ ህፃናትና ወጣቶች በራስ ላይ የሚበየኑትን እነዚህን ሰቅጣጭ ስንኞች ደጋግመው እየዘመሩ ወደ ውስጣቸው እንዲያሰርጿቸው ህወሓት ለረጅም ዓመታት ሳይታክት ሰርቷል፡፡

በመዝሙሩ ውስጥ ህጻናት ለተስፋ፣ለሰላም፣ለልማት፣ለአብሮነት፣ ለይቅርባይነት ለኢትዮጵያዊ ኩራት ቅንጣት ስፍራ እንዳይኖራቸው ይልቁንም በጠላትና በአውሬ እንደተከበቡ እንዲሰማቸው የሚያደርጉ ስንኞች ታጭቀዋል።

በዚህ ስሁት ፕሮፓጋንዳ ውስጥ ጦረኝነት፣ ደም አፋሳሽነት፣ ፍጹም ፅንፈኝነትና ጥላቻ፣ አልቦ እብሪተኝነት፣ ባሩድ ናፋቂነት፣ አጥፍቶ ጠፊነት ይሰበካሉ።ህፃናቱ ይህን የጥላቻና የደም ጎርፍ ጥሪም ከታች ከትምህርት ቤት ጀምረው እንዲዘምሩት ይደረጋሉ፡፡

የሽብር ቡድኑ አመራሮች የራሳቸውን ልጆችና ቤተሰቦች በውጭ አገራት በተንደላቀቀ ኑሮ እያኖሩ በትግራይ ወጣቶችና ህፃናት ውስጥ ጥላቻና ተስፋ ቢስነትን ይዘራሉ፤ለግማሽ ምእተ ዓመት ያህል ጥላቻን በትውልድ ቅብብሎሽ እንዲዳረስም ብዙ ርቀቶችን ተጉዘዋል፡፡

በትግራይ ተወላጆች ደምም በትረ ስልጣናቸውን አደላድለው ተቀምጠዋል፤ የሚፈልጉትም ዘርፈዋል፡፡

በትግራይ ትምህርት ቤቶች ሕጻናት እንዲዘምሩ የሚደረገው ትግራይን ስለማልማት ስላማሳደግ ከሌሎች ህዝቦች ጋር አብሮ ስለመኖር ሳይሆን በትግራይ ስም ለሚነግደው ዘራፊው የህወሓት ኢምፓየር የስልጣን ጥማት እርካታ የትግራይ ልጆች ደም እንደጎርፍ እንዲፈስ፤ሞተው አጥንታቸው ዱቄት ሆኖ እንዲበተንና ይህን በማድረግም አሸናፊዎች እንደሚሆኑ የሚሰብክ ነው፡፡

ይህም በዋናነት ወጣቶችን ለአጥፍቶ መጥፋት ሽብር በማነሳሳት እልቂትንና በማህበረሰቡ መካከል ኢ-ሞራላዊ መስተጋብር መፍጠርን ያለመ ነው፡፡

ንጹህ የትግራይ ህጻናትና ወጣቶችን በየቤታቸው፣ በየትምህርት ቤታቸው፣ ባስ ሲልም በየጫካው መዝሙሩን እንዲያጠኑ በማድረግ አዕምሯቸው ነገሮችን እንዳይመረምር ስለመልካም ነገሮች እንዳያስብ ለመሸሸጊያነቱ ያስተምራቸዋል።

የትግራይ ተወላጇ ወጣት ፍሬወይኒ ገብረጻዲቅ የሽብር ቡድኑ ይህን የጥላቻና የጦረኝነት ትርክት ከታች ጀምሮ እንዲሰርጽ መስራቱን ትናገራለች፡፡

ዘግናኝ ስንኝ በያዘ ጣፋጭ ዜማና በማር በተለወሰ መርዝ የትግራይ ህፃናትና ወጣቶች ደማቸውን እንዲያፈሱ ይሰበካሉ፡፡

እጅግ አስደንጋጭ የሆነውን መዝሙር እየሰሙም ሕጻናቱ ያድጋሉ፡፡ህወሓት ገደብ የሌለው የሥልጣንና የበቀል ጥሙን ለማርካት ሲል የሚያቆመው ተራራ እንደሌለ የማይሻገረው ወንዝም ከቶ ማንም ምድራዊ ሃይል እንደማያሸንፈው አልቦ እብሪቱን በተደጋጋሚ ይገልጻል።

በዚሁ መዝሙር “ለትግራይ ሕልውና ብቸኛው ጠበቃ እኔ ነኝ” እያለ በቅጥፈት፣በባዶ እብሪተኝነትና በስሁት ፕሮፓጋንዳ የትግራይን ህዝብ በጦርነትና በርሃብ ቀጥቷል።

ከጫካ ወደ መንበረ ስልጣን፤ከአገዛዝ ወደ አሸባሪ ቡድን እየተዋከበ ያለውና ሀገርን ለመበታተን እየተቅበዘበዘ የሚገኘው ይህ የሽብር ቡድን ስሁት ፕሮፓጋንዳውን ዛሬም አልቀየረውም።

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሙሉ ብርሃን ኃይሌ የትግራይ ወጣቶች ስለ ኢትዮጵያዊነት እንዳያስቡ፣ ስለ ሰላምና ስለ ልማት እንዳይወጥኑም በመዝሙሩ ኋላቀርና የፍረጃ ስንኞች አጥር መስራቱን ነው የሚናገሩት።

ቡድኑ እጅግ ጭካኔ የተሞላባቸው መልዕክቶችን በመዝሙር በማስተላለፍ በንጹሃን ደም ስልጣኑን ለማቆየት ስለመስራቱ ይናገራል፡፡

ለማይጠረቃው የስልጣን ጥሙና ሊያሳከው ስለሚፈልገው ንዋየ ፍቅሩ ህጻናትና ወጣቶች ሰባራ ክላሽንኮቭ እያወዛወዙ ገሚሱም በጀሌነት ወደ በረሃ እንዲግተለተሉ፣ አስገዳጅ በሆነ መልኩም የማይገባቸውን ዋጋ እንዲከፍሉ አድርጓል።

የሽብር ቡድኑ አቋሙንና የወደፊት ትልሙን ባነበረበት በዚህ የፕፓጋንዳ መዘሙሩ ውስጥ ስሁት እብሪተኝነቱን ብቻ ሳይሆን ህዝብን እንደ ማዕበል በግዳጅ አሰማርቶ በማስጨረስና ይህንንም “ህዝብ ነው ሀይላችን” በሚል በመግለፅ ድርሰቱን በገሃድ ህዝብ እያስጨረሰ አሳይቶበታል።

በእነዚህ ስንኞች ውስጥ ህወሃት ታዳጊዎችን ጨምሮ ወጣቶች ለሽብርና ለሀገር አፍራሽ ተልዕኮ ከፊት ይሰለፉለት ዘንድ ራሱን ፍጹምና አይበገሬ አድርጎ ስሏል።

የአሸባሪው ህወሃት ከግጭትና ጦርነት ወጪ እድሜውን ማራዘም እንደማይችል በመዝሙሩ ማሳየቱንም ነው አቶ ሙሉብርሃን የሚናገሩት፡፡

አሁንም “ህዝብ ነው ኃይላችን” በሚል መፈክር ህጻናትን በህዝባዊ ማዕበል ወደ ጦርነት እየማገደ ይገኛል፤ ይህንን እኩይ ተግባርም የሽብር ቡድኑ አፈቀላጤዎች በኩራት ሲናገሩት ይስተዋላል፡፡

ጥቂት የሽብር ቡድኑ ቁንጮ አመራሮች ሀገር ቁም ስቅሏን ሲያሳዩ፣ ሀብቷን ሲመዘብሩ ብዙዎችም የእነሱን ዓላማ ለማሳካት አካላቸውን አጥተው የሰው እጅ እንዲያዩ ተገደዋል።

ትግራይ የኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ ያላትን ያህል ከላይ የተጠቀሱት እብሪታዊ ስንኞች ግን የሽብር ቡድኑ ትግራይ ከአሸናፊነት ይልቅ እንድትገለልና በማያዋጣ ስሁት መንገድ ወደ ቁልቁለቱ እንድትገሰግስ አድርጓል።

የሽብር ቡድኑን ከፋፋይነት፣ ጸረ አንድነትና ፀረ ወንድማማችነት የፀና አቋም የሚያሳብቁ ፍጹም የጥላቻ ትርክቶች የታጨቁበት መልዕክትም አለው በመዝሙሩ ውስጥ።የህግ ባለሙያው አቶ ኪያ ጸጋዬ በሽብር ቡድኑ መዝሙሮችና የኪነ-ጥበብ ስራዎች የተካተቱ ሃሳቦች ግጭትን፣ጥላቻንና ማህበረሰባዊ አለመረጋጋቶችን የሚሰብኩ መሆናቸውን ያብራራሉ፡፡

የሽብር ቡድኑ ተከታዮቹን በፅንፍ ከኋላው ለማሰለፍም ሰዎችን “ሰው በላ የዱር አውሬ” አድርጎ እስከመሳል የደረሰ አገላለፅን በመዝሙሩ ተጠቅሟል።

የሰውን ልጅ ከጅብ እኩል ፈርጇል።የህወሃት አመራሮች በተንደላቀቀ ተድላ ውስጥ ህይወታቸውን መምራት እንጂ ሀገር ህዝብ ብሎ ነገር ደንታ እንደማይሰጣቸው እሙን ነው፡፡

ይህ ህልማቸው እንዲሳካ ደግሞ የትግራይ ህጻናት ጭምር ለመሰዋት ዝግጁ እንዲሆኑ ከጫካ ጀምረው ሰርተዋል፡፡በሽብር ቡድኑ አስገዳጅነት በጦርነት ያሰለፋቸው ህጻናትም ቡድኑ ለህጻናት ጭምር የሚራራ ማንነት እንደሌለው ነው የሚሰክሩት፡፡

ስጋቸውን አሞራ እንዲሻማው፣በየመንገዱና በየጥሻው ቀርተው እናቶቻቸው ከዓመት እስከ ዓመት የደም እንባ ቢያፈሱ ግድ ስለማይሰጠው የሰው ልጅ ሲሰማው አጥንት ድረስ የሚዘልቅ የጭካኔና ሽብር ፕሮፓጋንዳን እንዲህ ይለፍፋል።

ለእነሱ ስልጣን “ደም በምድሪቷ እንደጎርፍ እንዲፈስ” እለት ተእለት በመዝሙሩ ይታወጃል፡፡

የሽብር ቡድኑ በሚከተሉት ስንኞቹ ውስጥ ጦረኝነት፣ ሰላም ወዳድ አለመሆን፣ የድርጅቱና አመራሮቹ ባህሪ እንደኾነ ለመታዘብ ዕድል ይሰጣሉ።

የትግራይ ህዝብ ወንድምና እህት የሆኑና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያንን “ፋሽስት” በሚል ፍረጃ ህጻናትን ከልጅነት እድሜያቸው ጀምሮ የጠላትንት እሳቤን ይዘው እንዲያድጉ ያሰለጥናሉ፡፡

ይህ ሁሉ ለግማሽ ምእተ-ዓመት የዘለቀ የጥላቻ ግንብ ነው፤ ዓላማው ደግሞ በትግራይ ህዝብ ደም ስልጣን ላይ መቆየት ነው፡፡

በመሆኑም የትግራይ ህዝብ ይህንን በደም የሰከረ ቡድን ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወገኖቹ ጋር በመሆን ሊታገለው እንደሚገባ ነው አቶ ሙሉ ብርሃን ኃይሌ የተናገሩት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ ዐቢይ አሕመድ በአንድ ወቅት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደገለጹት፤ አሸባሪው ህወሃት ከትጥቅ ተግል ጀምሮ የትግራይን ህዝብ በጦርነት ለመማገድ ሲሰራ መቆየቱን መናገራቸው ይታወሳል፡፡

የሽብር ቡድኑ ለዘመናት በተከተለው የጥፋት መንገድ የትግራይ ህዝብ ለከፍተኛ ችግር እንደተዳረገ ጠቅሰው፤ የትግራይ ህዝብ ሰላምና ልማት እንጂ ጦርነት አይገባውም ነው ያሉት፡፡