የጠየመ መስከረም

203
አየለ ያረጋል /ኢዜአ/:-   በዘመን ቆጠራ ቀለበት ውስጥ ተውሳኳን 'የጳጉሜ ወርኅ' ለመሻገር ጉጉቱ ያይላል፤ መስከረም እስኪጠባ። መስከረም የወራት ሁሉ ቁንጮ ነውና። መስከረም ዘመን ያስረጃል፤ አዲስ ሕይወትና ተስፋ ደግሞ ይደግሳል። ደራሲ ካህሳይ ገብረ እግዚአብሔር "ቀዳማይ፣ ርዕሰ ክራሞት፣ መቅድመ አውርኅ፣ ርዕሰ ዐውደ ዓመት፣ የክረምት ጫፍ መካተቻ፣ የመፀው መባቻ" ይሉታል ወርኃ መስከረምን። የኢትዮጵያያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የባህር ሐሳብ ሊቃውንት መስከረም 1 ቀን ዓለም የተፈጠረበት፤ ኖኅ ከጥፋት ውኃ በኋላ ውሃው መጉደሉን ለማረጋገጥ ወደ ምድር የላካት እርግብ ቅጠል ይዛ የተመለሰችበት፣ እስራኤላዊያን ከግብጽ ባርነት ሲወጡ ቀይ ባሕርን የተሻገሩበት የብስራት ዕለት እንደሆነ ያነሳሉ። በእነዚና ሌሎች ኃይማኖታዊ ትውፊቶች ከጥንት ጀምሮ ነው መስከረም ለዘመን መለወጫነት የተመረጠው ይላሉ። ዕለቱም 'ርዕሰ ዓውደ ዓመት' ይሉታል። መስከረም ለመልክዓ ምድሩ፣ ለሰውና ለእንስሳት ሁሉ 'ፍስኃ ወተድላ' በማለት የደስታና የተድላ ወር መሆኑን አበው ይገልጻሉ። በመስከረም ምድር ትረጋለች፣ በአበቦች ታጌጣለች፣ በእንቁጣጣሽ ትፈካለች። ውኆች ይጠራሉ። በሰማዩ ሰማያዊ ላይ ብርሃን ይወጣል፤ የጥቁር ደመና ጋቢ ይገፈፋል፤ ክዋክብት በሰማይ ብረት ምጣድ ላይ መፈንጨት ይጀምራሉ። እጽዋትና አዝዕርት እንቡጦች ይፈነዳሉ። የመብረቅ ነጎድጓድ ተወግዶ የሰላምና የሲሳይ ዝናብ ይዘንባል። እንስሳት የጠራ ውሃ እየጠጡ፣ ለምለም ሳር እየነቸረፉ ይቦርቃሉ። እርሻ የከረሙ በሬዎች፣ ጭነት የከረሙ አህዮች መስከረም አንጻራዊ የእፎይታ ወርኃቸው ነው። ነጎድጓድ በአዕዋፋት ዝማሬ ይተካል። ንቦች አበባ ይቀስማሉ፤ ቀፏቸውን ያደራሉ። ቢራቢሮ ሳትቀር 'በመስከረም ብራ ከኔ በላይ ላሳር' ብላ ትከንፋለች። ለሰው ልጆች የመስከረም ደጅ ሲከፈት ግብዣው የትየሌለለ ነው። ምድር ብቻ አይደለችም በ’እንቁጣጣሽ’ የምትዋበው። መስከረም የሰው ልጆችም በተለይም ለወጣቶች የፍቅር፣ የእሸትና የአበባ ወር ነው። የሰላም፣ የንጹህ አየር፣ የጤና ድባብ ያረብብበታል። የጋመ በቆሎ እሸት ጥብስ፤ ቅቤ ልውስ፤ ቅቤ በረካ፤ መስቀል፣ ደመራ ይናፈቃል። የተጥፋፋ ይገናኛል። 'ሰኔ መጣና ነጣጠለን' ብለው ወርኃ ሰኔን የረገሙ ተማሪዎች ተናፋቂያቸውን ያገኛሉና 'መስከረም ለምለም' ብለው ያሞካሹታል። የገበሬው የሰብል ቡቃያ ያብባል፣ እሸት ያሽታል። ጉዝጓዝ ሣር፤ ትኩስ ቡና ይሸታል። 'መስከረም ሲጠባ ወደ አገሬ ልግባ …' እንዲሉ የተሰደዱት በአዲስ ዓመት መባቻ የአገራቸውን አፈር ያማትራሉ። የተጥፋፋ ይገናኛል። ’ኢዮሃ አበባዬ፤ መስከረም ጠባዬ’ የሚሉ ሕጻናት ተስፋና ምኞታቸውን በወረቀት ያቀልማሉ፤ የአበባ ስዕላት ይዘው በየደጃፉ ይሯሯጣሉ፣ የ’እደጉ’ ምርቃት ያገኛሉ፤ በደስታ ይንቦጫረቃሉ። በዚህ ድባብ ነው እንግዲ መስከረምን የግዑዛንም የሕይወታውያንም የነፃነት፣ የተስፋና የፍቅር ወርኅ ተደርጎ የሚናፈቀው። ዛሬ አዲስ ዓመት ላይ እንገኛለን። 2011 ዓ.ም ከገባ ገና ስምንት ቀናት ብቻ ተቆጠሩ። በአገራችን የፖለቲካ ታሪክ ዑደት ውስጥ መስከረም ያሰናበተው የ2010 ዓመት ብዙ መልኮች እንደነበሩት ይታወሳል። የሞትና የመፈናቀል ዜናዎችን በተጓዳኝ በፖለቲካ ምህዳር ላይ በርካታ ድንቅ ጉዳዮች የተከናወኑበት ጉራማይሌ ዓመት ነበር። 'ፍቅር፣ ይቅርታ፣ አንድነትና መደመር' ጽንሰ ሃሳቦች በተግባር ደረጃ የተጀማመሩበት፤ የወደፊት የአገራችን ጉዞ የተስተካከለ እንደሚሆን ተስፋ የተጣለበት ዓመት ነበር። ወደ መንበረ ስልጣን ከመጡ መንፈቀ ዓመት ያስቆጠሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶክተር) በድንቅ ፍጥነት፣ በውጭና በአገር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያዊያንን በድጋፍ ሰልፍ ያነቃነቁ እርምጃዎችን ወስደዋል። እናም ባለፈው ሳምንት የባተው አዲሱ ዓመት ልዩ ባህሪ ነበረው። ይኸውም ለ27 ዓመታትና ከዛ በላይ በፖለቲካውም ሆነ በኃይማኖት መስኮች ተኳርፈው የነበሩ ወገኖችን ተቀራርበው በዋዜማው እንደ ቤተሰብ በአንድ መዓድ መቁረሳቸው ነው። በትጥቅ ትግልም ሆነ በሌላ መንገድ በውጭ አገሮች የነበሩ ግለሰቦችና ድርጅቶች 'መስከረም ሲጠባ፤ ወደ አገሬ ልግባ' በሚመስል መልኩ ወደ አገር ቤት የተመሙበት መስከረም ነበር። እናም ወርኃ መስከረም እንኳንስ እነዚህ ለየት ያሉ ትዕይንቶች ተስተናግደውበት በተፈጥሮው 'ወርኃ ፍስሃ' ነውና በብዙኃኑ ኢትዮጵያዊያን ዘንድም ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ነበር። በአንድነትና በብሔር ፖለቲካ ገመድ 'ወዲህ ወዲያ' ለምትላጋው ኢትዮጵያ ቀጣይ እጣ ፈንታ ብሩህ እንዲሆን ብዙዎች መልካም ምኞታቸውን የገለጹበት ዐውደ ዓመት ነበር። በበዓሉ ዋዜማ በሚሌኒየም አዳራሽ በነበረው የአዲስ ዓመት ማብሰሪያ ምሽትም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከሌሎች ባለስልጣናትና ኃይማኖት መሪዎች ባሻገር አስተያይታቸውን ሲሰጡ የነበሩ ተሳታፊ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተስፋና ምኞታቸውን ሲገልጹ ተስተውለዋል። ተናፋቂው መስከረም በባተ ሳልስት ግን የመልካም ምኞት መግለጫዎች ተነበው ሳያልቁ፣ የህጻናት አበባ ስዕላት ቀለማቸው ሳይደርቅ፣ የዓውደ ዓመት ድግስ ሞሰቦች ሳይከደኑ በአገሪቱ ዋና ከተማ፣ በአፍሪካ ሕብረት መናገሻ፣ በዓለም አቀፍ ተቋማትና ዲፕሎማሲ ከተማዋ አዲስ አበባ የደስታው ድባብ ዳመነ። ቀለል ባሉ ንትርኮች የተጀመረ የአስተሳስብ ተቃርኖ መስከረም ሶስት፣ አራትና አምስት በከተማዋ በርካታ አካባቢዎች ተዳርሶ የከተማዋ ብቻ ሳይሆን የአገር ጉዳይ ሆኖ ሰነበተ። የአዲሱን ዓመት መልካም ምኞት ያበሰሩ የመንግስት ባለስልጣናት የግጭት ዜናዎች መግለጫ ሰጭዎች ሆነው ሰነበቱ። ግጭቱ መልኩን ቀይሮም በከተማዋ ዙሪያ ባሉ ከተሞች በተፈጠረ ሁከትና ትርምስ ግድያ፣ ዘረፋና መፈናቀል አስከተለ። የድርጊቱ አስነዋሪነት ደግሞ አገራዊ ለውጡን ደግፈው በወጡ ወገኖች ላይ ቅሬታ አሳደረ። ድርጊቱን ያወገዙ አዲስ አበቤዎችም "ፍትህን በመሻት፤ ስርዓት አልበኝነትን በመቃወም" ትናንት ጎዳናዎችን አጥለቀለቁ። በሰልፉ ላይ በተፈጠሩ የሰልፈኞችና የጸጥታ ኃይሎች ግጭትም ሌላ የሰው ሕይወት በሰልፍ ላይ ተቀጠፈ። በዚህም 'ወርኃ ፍስሃው' መስከረም የፈካ ገጹ ጠየመ። እርስ በርስ መገዳደል፣ መናቆር፣ ዘረኝነት፣ ጥላቻ ግንቦች ፈርሰው 'የአንድነትና የፍቅር 2011' የተመኘች ኢትዮጵያ ገና ጉዞዋን ስትጀምር እንቅፋት መታት። ዛሬም የሚያስተዳድራት መንግስት አዲሱን ዓመት ደስታ ማጣጣም ሳይሆን 'አገራዊ ሁኔታው እንዴት ይረጋጋ' በሚሉና ድርጊቱን በሚያወግዙ ጉዳዮች ላይ ተጠምዷል። የጥቃቱ ሰለባ በመሆን ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉት የቡራዩ፣ ከታ፣ ፊሊዶሮ፣ አንፎና ሌሎች አካባቢዎች ነዋሪዎች ቤታቸውን ወደኋላ ትተው ሸሽተው በተጠለሉባቸው ስፍራዎች ህብረተሰቡ አይዟችሁ እያለ ነው። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ይህን ችግር ለመወጣት ኮሚቴ አቋቁሞ ወደተግባር ገብቷል። የኦሮሚያ ክልል መንግስትም ኃላፊነት በመውሰድ የተፈናቀሉትን ወደቀዬአቸው ለመመለስ እንደሚሰራ ቃል ገብቷል። በጥቃቱ ተፈናቅለው የሚገኙትን ዜጎች የጎበኙ የመንግስት ሹማምንቶች አጥፊዎችን በማደን ለፍርድ እንደሚያቀርቡና ዳግም ተመሳሳይ ቀውስ እንዳይከሰት ለመስራት ያላቸውን ዝግጁነት መግለጻቸውም የጨለመውን ተስፋ ያለመልማል። የተነገረው ወደተግባር ይለወጥ ዘንድ መስራት የግድ ይላል። 'ፈክቶ የጠየመ መስከረም ወደ ክብሩ እንዲመለስ፤ የአገሪቱ ተስፋም ዳግም እንዳይጨለም' ምኞቴ ነው!!  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም