አሸባሪው ህወሓት ዕድሜያቸው ያልደረሰ ህፃናትን በጦርነት በማሰለፍ ወንጀል እየፈጸመ ነው -የሀዲያ ዞን ሴቶች

203

ሆሳዕና፣ ነሀሴ 24 ቀን 2014 (ኢዜአ) አሸባሪው የህወሓት ቡድን ዕድሜያቸው ያልደረሰ ህፃናትን በጦርነት በማሰለፍ እየፈጸመ ያለውን ወንጀል አለማቀፍ የህጻናት መብት ጭምር የጣሰ በመሆኑ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊያወግዘው እንደሚገባ የሀድያ ዞን ሴቶች ገለጹ።

የዞኑ ሴቶች በአሸባሪው የህወሓት ቡድን ለ3ኛ ጊዜ የተከፈተውን ጦርነት የሚያወግዝ ሰልፍ ዛሬ በሆሳዕና ከተማ አካሂደዋል።

እድሜያቸው ያልደረሰ ታዳጊዎችን ወደ ጦርነት በመማገድ ህወሃት አለማቀፍ ህግን ጭምር የጣሰ በመሆኑ ከድርጊቱ እንዲታቀብ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብና ድርጅቶች ጭምር ሊያወግዙት ይገባል ብለዋል።

ወይዘሮ ከበቡሽ አማረ እንዳሉት ቡድኑ የሰላም አማራጭን ወደ ጎን በመተው ጦርነትን መምረጡ ከግጭት ውጪ መኖር እንደማይችል ያሳያል።

የአሸባሪው ቡድን መሪዎች ልጆቻቸውን በአውሮፓና አሜሪካ እያኖሩ ለትግራይ ህዝብ ተቆርቋሪ በመምሰል ምንም የማያውቁ ታዳጊ ህጻናትን ወደ ጦር ሜዳ እየማገዱ ይቅር የማይባል ወንጀል እየፈጸሙ ነው ብለዋል።

ቡድኑ ሀገሪቱን በመራበት ዘመን በዜጎች ላይ የፈፀመው የጭካኔ ተግባር ታሪክ የማይረሳው ነው ያሉት ደግሞ የሰልፉ ተሳታፊ ወይዘሮ እንዳሻሽ ፀጋዬ ናቸው።

በአሁኑ ወቅትም ችግሮች በሰላም እንዲቋጩ በመንግስት የቀረበውን አማራጭ በመተው እድሜአቸው ያልደረሱ ልጆችን ወደ ጦርነት እየማገደ በመሆኑ መላው አለም ድርጊቱን ሊኮንነው ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

ቡድኑ እድሜያቸው ያልደረሱ ልጆች ጫንቃ ላይ የጦር መሳሪያ በማሸከም ለጦርነት ማሰለፉ የህጻናት መብትና ስነልቦና ጭምር የሚጎዳ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የህዝቡን ሰላምና እድገት የማይፈልገውን ቡድኑ የጥፋት መንገድ ለማምከን በመንግስት እየተወሰደ ያለው እርምጃ እንደሚደግፉ ተናግረዋል።

በሀድያ ዞን የብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካና ርዮት አለም ዘርፍ ኃላፊ አቶ ከይረዲን ራመቶ እንዳሉት የሰላም አማራጭን እምቢ በማለት ህወሓት ለሶስተኛ ዙር ጦርነት ማወጁ ካለው የስልጣን ጥም ስካርና ጭካኔ የመነጨ ነው ብለዋል።

"መንግስት ለሀገር ሰላም በተለይም በአሸባሪው ህወሓት ተጽዕኖ ስር ነጻነቱን ተነፍጎ ለሚኖረው ለትግራይ ህዝብ ጥቅም የሰላም አማራጭ በተደጋጋሚ ቢያቀርብም እምቢታን የመረጠው ቡድኑ ከራሱ ፍላጎት በተጨማሪ ከጋላቢዎች ተልዕኮ በመነጨ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

ተምረው ለሀገር ኩራት ለቤተሰብ ደጀን መሆን የሚችሉ ህጻናትን መሳሪያ አሸክሞ ጦር ሜዳ በማሰለፍ ዓለም አቀፍ ህግን ከመጣስ ባለፈ በትውልዱ ላይ እየፈጸመ ላለው ግፍ ሊጠየቅ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ቡድኑ በክልሉ ህፃናት ላይ እያደረሰ የሚገኘውን በደል የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊያወግዘውና በህግ እንዲጠየቅ መሰራት አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም