በክልሉ 248 ሺህ ሄክታር መሬት በአኩሪ አተር ሰብል እየለማ ነው- ቢሮው

323

ባህርዳር፤ ነሐሴ 24/2014 (ኢዜአ)፡ በአማራ ክልል ለውጭ ምንዛሬ ግኝትና ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚውል የአኩሪ አተር ሰብል በ248 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ እየለማ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በምዕራብ ጎንደር ዞን በአኩሪ አተር የለማ ሰብል በፌዴራል፣ በክልልና በዞን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና በዘርፉ ባለሙያዎች ትላንት ተጎብኝቷል።

የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ኃይለማርያም ከፍያለው በጉብኝቱ ወቅት እንደገለጹት መንግስት ለውጭ ምንዛሬ ግኝትና የኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚውሉ ሰብሎችን በብዛትና በጥራት እንዲመረቱ ያስቀመጠውን አቅጣጫ ለማሳካት ቢሮው በትኩረት እየሰራ ነው።

ለዚህም በ2014/2015 የምርት ዘመን በክልሉ 250 ሺህ ሄክታር መሬት በአኩሪ አተር ሰብል ለማልማት ታቅዶ የዕቅዱን 99 በመቶ ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል።

ከዚሁ መሬትም ከግማሽ በላይ የሚሆነው በምዕራብ ጎንደር ዞን የለማ መሆኑን ጠቅሰዋል።

''የአኩሪ አተር ልማትን በትኩረት በመስራት ውጤት ማምጣት ችለናል'' ያሉት ዶክተር ኃይለማርያም፤  በአማካኝ በሄክታር 30 ኩንታል ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅም አስታውቀዋል።

በግብርና ሚኒስቴር የእርሻና ሆልቲካልቸር ልማት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር መለስ መኮንን በበኩላቸው በምርት ዘመኑ በአማራ ክልል በስፋት እየለማ ያለውን የአኩሪ አተር ሰብል ወደ ኦሮሚያ፣ ጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝና ደቡብ ክልሎች በቀጣይ ለማስፋፋት ሚኒስቴሩ በትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ለኤክስፖርት የሚሆንና የኢንዱስትሪዎችን የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ 250 ሺህ ሄክታር መሬት በአኩሪ አተር እያለማ መሆኑን አመልክተው፤ ከዚህ ውስጥም ከግማሽ የሚበልጠው መሬት በምዕራብ ጎንደር ዞን በኩታ ገጠም የእርሻ ማሳ እየለማ መሆኑን መመልከታቸውን አረጋግጠዋል።

 በቀጣይም የአኩሪ አተር ልማት እንዲስፋፋ  በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ  አስታውቀዋል።

በዞኑ ከ17 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችና ባለሀብቶች በአኩሪ አተር ልማት እየተሳተፉ ነው ያሉት ደግሞ የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና  አስተዳዳሪ አቶ ቢክስ ወርቄ ናቸው።

80 ሺህ ሄክታር መሬት በአኩሪ አተር ሰብል ለማልማት ተቅዶ  ከዕቅድ በላይ 127 ሺህ ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም ማልማት እንደተቻለም አስረድተዋል።

በዞኑ በስፋት እየለማ ካለው የአኩሪ አተርና የሰሊጥ ሰብል ከ3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።

 በዞኑ መተማ ወረዳ በ2012 ዓ.ም 200 ሄክታር መሬት ወስደው በእርሻ ኢንቨስትመንት ዘርፍ መሰማራታቸውን የተናገሩት ደግሞ አቶ አበበ ውለታው ናቸው።

 የወሰዱትን የእርሻ መሬት ግማሹን በአኩሪ አተር ሰብል፣ ግማሹን ደግሞ በጥጥ  በመሸፈን እያለሙ መሆናቸውን አስረድተዋል።

''የአኩሪ አተር ሰብል ዘንድሮ በስፋት እየተመረተ በመሆኑ መንግስት የገበያ ችግር እንዳይገጥመን ከኢንዱስትሪዎች ጋር ከወዲሁ ሊያስተሳስረን ይገባል'' ብለዋል።

በዚሁ ወረዳ በደለሎ ፋና ቀበሌ በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩት አርሶ አደር ይትባረክ ልዑል በበኩላቸው የተከረከቡትን 69 ሄክታር በአኩሪ አተር፣ በሰሊጥና ማሽላ ሰብሎች ሸፍነው እያለሙ መሆኑን ተናግረዋል።

ተደራጅተን በአንድ እጃችን ማረሻ፣ በአንድ እጃችን መሳሪያ ይዘን የአካባቢያችንን ሰላም እየጠበቅን የልማት ስራችንን እያከናወንን እንገኛለን ሲሉም አስረድተዋል።

''ለዳግም ወረራ የመጣውን አሸባሪው  በመጣበት ለመመለስም ተደራጅተን አካባቢያችንን እያለማንና  ነቅተን እየጠበቅን ነው'' ብለዋል።

በክልሉ በ2014/2015 የምርት ዘመን ከ4 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር የሚበልጥ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ተሸፍኖ እየለማ  መሆኑን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም