የሚዲያና ኮሙኒኬሽን የቀውስ ጊዜ ዘገባና የመረጃ ስርአት በጥንቃቄ መመራት ይኖርበታል

543

 ነሐሴ 22 ቀን 2014 (ኢዜአ)  የሚዲያና የኮሙኒኬሽን ተቋማት የቀውስ ጊዜ ዘገባና የመረጃ ተደራሽነት ብሄራዊ ጥቅምን ታሳቢ ያደረገና በጥንቃቄ የሚመራ ሊሆን እንደሚገባ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አሳሰበ።

ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የነበረው የፌዴራልና የክልል የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ጉባኤ ተጠናቋል።

ጉባዔው የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፣ የፌዴራልና የክልል የኮሙኒኬሽን ዘርፎች የ2014 በጀት ዓመት የስራ አፈጸጻምና የ2015 ዕቅድ ላይ ተወያይቷል።

የመንግስት ኮሙኒኬሸን የቀጣይ 5 ዓመታት ረቂቅ ስትራቴጂ ሰነድ እንደሁም በመንግስት ኮሙኒኬሸንና የክልል የዘርፉ መዋቅሮች የስራ ግንኙንት ላይ በተዘጋጀ የመግባቢያ ሰነድ ላይም መክሯል።

የክልል ኮሙኒኬሽን ተቋማት በፌዴራል መንግስት የሚገለጹ መረጃዎችን የሚለቁበት አግባብ የአሰራር ስርዓት ሊዘረጋለት እንደሚገባም በጉባኤው ተመልክቷል።

የክልል የኮሙኒኬሸን መዋቅሮች ያልተናበቡ መረጃዎችን ከመስጠት እንዲቆጠቡና ፈቃድ ያልተሰጣቸው ሚዲያዎች በመንግስት ሁነቶች ላይ የሚሳተፉበት ዕድልም ሊስተካከል ይገባል ነው ያሉት።

በተለይ አገር ቀውስ ሲገጥማት የሚዲያና ኮሙኒኬሸን ዘርፉ ላይ ያለው የመረጃ ፍሰት ጥንቃቄ ይሻል ብለዋል።

የክልል ሚዲያዎች ከክልላቸው ባሻገር ወደ ሌሎችም ክልሎች ተደራሽነታቸውን በማስፋት በአገራዊ መግባባትና ሕብረ ብሔራዊ አንድነት ላይ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም ጠቅሰዋል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ ቱሉ፤ ለአገርና ህዝብ ጥቅም ሲባል የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ እንዲጠናከር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።

የአዘጋገብና መረጃ አሰጣጥ ሂደት ፈጣንና በዘመነ መልኩ ከወቅቱ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች እንደየ ዐውዱ እየተቃኘ መራመድ ይኖርበታልም ነው ያሉት።

ጠንካራ ኮሙኒኬሽን ስርዓት ለመገንባት የሚያስችል የኮሙኒኬሽን ፖሊሲና ስትራቴጂ ዝግጅት እየተጠናቀቀ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።

የክልል ኮሙኒኬሽን ተቋማት በተቀናጀ አገራዊ አጀንዳ እየተናበቡ መስራት እንዳለባቸው ጠቅሰው በተናጠል አጀንዳ ቀርጾ ማስተጋባት የለባቸውም ብለዋል።

በመሆኑም በፌዴራል መንግስት በኩል ሊሰራጩ የሚገባቸው ጉዳዮች ላይ መረጃ ከመስጠት ሊቆጠቡ ይገባል ነው ያሉት።

በተለይም የቀውስ ጊዜ የኮሙኒኬሽን ስራ ልዩ ትኩረት ይሻል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ጉዳዩ ከሚመለከተው አገራዊ ተቋምና ኮሚቴ በስተቀር ከጦርነት ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ማሰራጨት አይችሉም ነው ያሉት።

በእንዲህ አይነት ወቅት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ስራዎች የአገርን ብሔራዊ ጥቅም ታሳቢ ባደረገ መልኩ መመራት አለባቸው ብለዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ የቀውስ ጊዜ አዘጋገብ መመሪያዎች የተዘጋጁ በመሆኑ በቀጣይ ይፋ የሚደረጉ ይሆናል።

የአገልግሎቱ ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ደሲሳ፤ የህዝብ መረጃ የማግኘት መብት መገደብ ስለሌበት ተቋማት በየወቅቱ ለሚዲያዎች መረጃ መስጠት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

በተቋማት ላይ ጠንካራ የምርመራ ጋዜጠኝነት እንዲሰራ የመንግስት ጽኑ ፍላጎት መሆኑን ጠቅሰው ከወዲሁ ግልጽ መረጃ ለመስጠት መዘጋጀት አለባቸው ነው ያሉት።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎትም ከክልሎች ጋር ደረጃውን በጠበቀና ወጥነት ባለው አግባብ ተናቦ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።