ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ከአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ

86
አዲስ አበባ ግንቦት 11/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ ጋር በስልክ ተወያዩ። የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ፍጹም አረጋ በትዊተር ገጻቸው እንዳስነበቡት፤ ውይይታቸው በዋናነት በሁለትዮሽ ግንኙነት፣ በቀጠናው ሰላምና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው። አሜሪካና ኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅምን ያስጠበቀና ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ስትራቴጂካዊ ግንኙነት አላቸው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ በሳዑዲ አረቢያ የተሳካ ጉብኝት ካደረጉ በኋላ በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ በመገኘት ከአገሪቱ አልጋወራሽ ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ ጋር የሁለቱ አገራት ግንኙነት በሚጠናከርበት ጉዳይ ዙሪያ መምከራቸውን ጠቅሰዋል። በሳዑዲ አረቢያ በነበራቸው ቆይታም 900 ወንዶችና 100 ሴቶች በአጠቃላይ አንድ ሺህ ኢትዮጵያውያን እስረኞች እንዲፈቱ ማድረጋቸውንና፤ ከነዚህ መካከል 60ዎቹ በቀጣይ ሶስት ቀናት ቀሪዎቹ ደግሞ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ወደ አገራቸው ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የሳዑዲው አልጋወራሽ ልዑል መሀመድ ቢን ሰልማን ለእስረኞቹ መፈታት ላደረጉት ቀና ትብብር የጠቅላይ ሚንስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊው አቶ ፍጹም አረጋ ምስጋና አቅርበዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም