የክረምቱ ዝናብ በቀጣይም ከባድ ዝናብና ቅፅበታዊ ጎርፍ ሊያስከትል ስለሚችል ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል

118

ነሐሴ 17 ቀን 2014 (ኢዜአ)የክረምቱ ዝናብ በቀጣይም በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች ከባድ ዝናብና ቅፅበታዊ ጎርፍ ሊያስከትል ስለሚችል ጥንቃቄ እንዲደረግ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳሰበ።

በኢንስቲትዩቱ የአየር ሁኔታና የአየር ጠባይ ትንበያ ባለሙያ ታምሩ ከበደ እንደሚሉት የዘንድሮው ክረምት በላሊና ተፅዕኖ ስር የወደቀ ሆኗል።በዚህም ባለፉት ሁለት ወራት በተለይ በሰሜናዊ የአገሪቱ አጋማሽ ባሉ ቦታዎች ላይ ለቅፅበታዊ ጎርፍና ለወንዞች ሙላት መንስኤ የሆነ ከባድ ዝናብ እንደነበር ጠቅሰዋል።

በክረምቱ በመደበኛ ሁኔታ የዝናብ ሁኔታው ቀጣይነት ስለሚኖረው በአንዳንድ አካባቢዎች የመሬት መንሸራተት ሊኖር እንደሚችልም ጠቁመዋል።በመሆኑም በተለይ በወንዞች አካባቢ፣ በተዳፋት፣ ቁልቁለታማና ዳገታማ ቦታዎች ላይ የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች ከወዲሁ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በክረምቱ በፀሀይ ኃይል በመታገዝ የሚፈጠሩ ደመናዎችም እንዲሁ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ እንዲኖር እንደሚያደርጉ ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት እየተመዘገበ ያለው የአየር ሁኔታም በዚሁ ሳቢያ የመጣ ስለመሆኑ አስረድተዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች በረዶና መብረቅ የቀላቀለ ነጎድጓዳማ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል አመላክተዋል።የዝናቡ ሁኔታ በነሃሴ ወር የመጨረሻዎቹ ቀናት ሰሜን ምስራቅ የአገሪቱ አካባቢዎች በመደበኛ ሁኔታ እየቀነሰ እንደሚሔድ ገልፀዋል።በሌሎች የአገሪቷ አካባቢዎች ግን የዝናቡ ሁኔታ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሚያሳይ ትንበያ መኖሩን ባለሙያው ጠቁመዋል።

በዚህ መሰረት በምዕራብና ደቡብ ምዕራብ፣ጋምቤላ፣ ምዕራብ ኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝና መካከለኛው የአገሪቱ አካባቢዎች ዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ክስተቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የክረምት ወቅት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ አካባቢዎች በሚኖረው የዝናብ ሁኔታ በርካታ ቦታዎች ላይ የጎርፍ መከሰት ሊኖር ይችላልም ነው ያሉት።በመሆኑም ከፍተኛ ዝናብ እያገኙ ባሉ የመኸር አብቃይ አካባቢዎች የግብርና ባለሙያዎችና አርሶ አደሮች በየእለቱ ማሳቸውን መከታተልና ውሃ እንዳይተኛ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

የዝናቡ ሁኔታ መጨመር በሌላ በኩል ለሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ሀይቆች የውሃ መጠን መጨመር አዎንታዊ ሚና የሚኖረው መሆኑንም አመላክተዋል።በክረምቱ በምዕራብና ደቡብ ምዕራብ፣ በጋምቤላ፣ በምዕራብ ኦሮሚያ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝና በመካከለኛው የአገሪቱ አካባቢዎች ዝናብ ሰጪ ክስተቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም