አዲስ አበባን የሁከት ቀጠና ለማድረግ የሚሰሩ ኃይሎችን ሴራ በማክሸፍ አስተማማኝ ሰላም የሚያስጠበቅ የጸጥታ ኃይል እየተገነባ ነው

161

ነሐሴ 17 ቀን 2014 (ኢዜአ)አዲስ አበባን የሁከት ቀጠና ለማድረግ የሚሰሩ ኃይሎችን ሴራ በማክሸፍ አስተማማኝ ሰላም የሚያስጠበቅ የጸጥታ ኃይል እየተገነባ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቀንአ ያደታ ገለጹ፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለአራት ወራት ያሰለሰናቸውን 26ኛ ዙር የመደበኛ ፖሊስ አባላት አስመርቋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቀነአ ያደታ በዚሁ ጊዜ አዲስ አበባ የተለያዩ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ እንዲሁም የመቻቻልና የኢትዮጵያዊነት ተምሳሌት ከተማ መሆኗን ተናግረዋል።

እንደ አሸባሪው ህወሃትና ሸኔ ያሉ የጥፋት ኃይሎች አዲስ አበባን የሁከት ቀጠና በማድረግ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ዓላማ ሰንቀው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም የአዲስ አበባ ፖሊስ የጥፋት ኃይሎችን እኩይ ዓላማ ለማክሸፍ በክህሎትና እውቀት ዝግጁ መሆን አለባቸው ነው ያሉት፡፡ተመራቂ የፖሊስ አባላት በስልጠና ወቅት ያገኙትን እውቀትና ክህሎት እንዲሁም ከነባር ፖሊሶች ልምድ በመቅስም በእኩልነት ለማገልገል ሁሌም ዝግጁ መሆን እንዳለባቸውም አንስተዋል፡፡

May be an image of 6 people and sky

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አመራሮችም ተመራቂ የፖሊስ አባላት ወንጀልን መከላከልና የህዝብ ደህንነት ማስጠበቅ እንዲችሉ የሚጠበቅባቸውን እገዛ እንዲያደርጉም አሳስበዋል።

ፖሊስ ወንጀልን ለመከላከልና በልዩ ልዩ የልማት እንቅስቃሴዎች ላይ መሳተፍ አለበት ያሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ናቸው።

አዲስ አበባ ፖሊስ በመዲናዋ የተከናወኑ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ መድረኮች በፍጹም ሰላም እንዲካሄዱ ከፍተኛ ሚና ማበርከታቸውንም አንስተዋል፡፡ፖሊስ መዲናዋን ዘወትር ነቅቶ በመጠበቅ በርካታ የጥፋት ሴራዎችን ማክሸፍ መቻሉንም እንዲሁ፡፡

በተወሰዱ ኦፕሬሽኖችም ለጥፋት ዓላማ ሊውሉ የነበሩ የተለያዩ መሳሪያዎችን፣ተተኳሾችን፣ተቀጣጣይ መሳሪያዎችን ከእነተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስራ ማዋል መቻሉን ገልጸዋል።

በቀጣይም ወንጀልን በመከላከል የከተማዋን ሰላምና ጸጥታ አስተማማኝ ለማድረግ ከህብረተሰቡ ጋር መተባበር ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም