የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከካርቱም አዲስ አበባ ሲጓዝ በነበረው አውሮፕላን ከተፈጠረው ክስተት ጋር በተያያዘ ምርምራ ማድረግ መጀመሩን ገለጸ

ነሐሴ 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ከካርቱም አዲስ አበባ ሲጓዝ በነበረው አውሮፕላን ከተፈጠረው ክስተት ጋር በተያያዘ ምርምራ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ።

ሰኞ ነሐሴ 9 ቀን 2014 ዓ.ም ከሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም ወደ አዲስ አበባ ሲጓዝ  የነበረ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር ET343 የሆነ የመንገደኞች አውሮፕላን አዲስ አበባ ካለው የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ማዕከል ጋር ያለው ግንኙነት ተቋርጦ እንደነበር የሚያመላክት መረጃ እንደደረሰው አየር መንገዱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

አውሮፕላኑ አዲስ አበባ ከሚገኘው የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ማዕከል ጋር የነበረው ግንኙነት በድጋሚ ከተመለሰ በኋላ በሰላም ማረፉን አመልክቷል።

ከተፈጠረው ሁኔታ ጋር  በተያያዘም የአውሮፕላኑ የበረራ ሰራተኞች ተጨማሪ ምርመራ እስኪደረግባቸው ድረስ ለጊዜው ከስራ መታገዳቸውን ገልጿል።

አየር መንገዱ የምርመራ ውጤቱን መሰረት በማድረግ ተገቢውን እርምጃ እንደሚወስድ ነው በመግለጫው ያመለከተው።

በተፈጠረው ክስተት ዙሪያ አየር መንገዱ በቀጣይ ዝርዝር መረጃዎችን እንደሚያሳውቅ ጠቁሟል።

“የደንበኞችን ደህንነት ማስጠበቅ ቅድሚያ ትኩረቱ ነው ወደፊትም ይሄው ተግባሩ  ይቀጥላል ” ሲል አየር መንገዱ በመግለጫው አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም