አንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ቤተ መጽሀፍት የተለያዩ ይዘት ያላቸውን መጽሀፍት አበረከተ

329

ነሀሴ 14/2014 /ኢዜአ/አንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ቤተ መጽሀፍት የተለያዩ ይዘት ያላቸውን መጽሀፍት አበረከተ፡፡

አርቲስቱ ድጋፍ ያደረጉት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አዲስ ባስገነባው የሚዲያ ኮምፕሌክስ ውስጥ በተደራጀ መልኩ ለሚቋቋመው ቤተመጽሀፍት መሆኑንም ተናግሯል፡፡

መጽሃፍቱንም ለተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ አስረክቧል፡፡

የኢትዮጵይ ዜና አገልግሎት ላለፉት 80 ዓመታት መረጃን ሰንዶ ለህዝብ ተደራሽ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና ማበርከቱንም አስታውሷል፡፡

ተቋሙ መረጃን ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር በዘርፉ ብቁ የሆነ የሰው ኃይል መያዝ እንደሚጠበቅበት ጠቅሶ፤ ለዚህ ደግሞ የተቋሙ ቤተ መጽሃፍት ወቅቱን በሚመጥን መልኩ ሊደራጅ ይገባል ነው ያለው፡፡

ከዚህ አኳያ ዛሬ ያበረከተው መጽሃፍ የተቋሙ ቤተ መጽሃፍት በግብዓት በማሟላት ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖራቸው ያላቸውን እምነት ገልጿል፡፡

መጽሀፍቶቹ ከአቶ አንዱዓለም አበበ እና ባለቤታቸው ወይዘሮ እሌኒ ፀጋዬ የተገኘ እንደሆነም ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋናስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው፤ አርቲስቱ ላደረገው የመጽሃፍት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አሁን ላይ ከዋና መስሪያ ቤቱ ባሻገር በአገር አቀፍ ደረጃ ባሉት 38 ቅርንጫፎች አመካኝነት መረጃን ተደራሽ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪ የስልጠና ማዕከላትን በማቋቋም በዘርፉ ብቁ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡