ኢትዮጵያ የአልሸባብ የሽብር ቡድንን ለማስወገድ የምታደርገውን ጥረት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊደግፍ ይገባል

117

ነሐሴ 13 ቀን 2014(ኢዜአ) ኢትዮጵያ የአልሸባብ የሽብር ቡድንን ለማስወገድ የምታደርገውን ጥረት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊደግፈው እንደሚገባ በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሄኖክ ተፈራ ገለጹ፡፡

በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሄኖክ ተፈራ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ አልሸባብ ለቀጠናው የሰላምና ደህንነት አደጋ መሆኑን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊገነዘበው ይገባል ነው ያሉት፡፡

በመሆኑም የሽብር ቡድኑን ለማስወገድ በሀገራት መካከል ያለው ትብብር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ አልሸባብን በመዋጋት ረገድ የበኩሏን ሚና ስትወጣ መቆየቷን የጠቀሱት አምባሳደር ሄኖክ፤ ከዚህ አኳያ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የኢትዮጵያን ጥረት ሊደግፍ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

ከሰሞኑን የኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች በምስራቁ የኢትዮጵያ ክፍል ወደ አገር ውስጥ ሰርጎ ለመግባት በሞከረው የአልሸባብ የሽብር ቡድን ላይ በወሰዱት እርምጃ የሽብር ቡድኑ ከፍተኛ ኪሳራ እንደገጠመው አስታውሰዋል፡፡

ይህም የሽብር ቡድኑ በሶማሊያ ብቻ ሳይሆን የቀጠናው ስጋት መሆኑን እንደሚያመላክት ገልጸው፤ የሽብር ቡድኑን ለማስወገድ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ትብብሮች እንደሚያስፈልጉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይሎች በተለያዩ አካባቢዎች ወደ ኢትዮጵያ ሰርጎ ለመግባት በሞከረው የአልሸባብ የሽብር ቡድን ላይ በወሰዱት እርምጃ የሽብር ቡድኑ ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራዎች እንደገጠሙት ይታወሳል፡፡

የጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃም የአልሻባብ የቅስቀሳና ፕሮፓጋንዳ ኃላፊ ፉአድ መሐመድ ከሌፍ (ሼንጎሌ)፣ የሽብር ቡድኑ ቃል አቀባይ አብዱላዚዝ አቡ ሙሳ፣የአልሸባብ የቦኮል ዞንና የኢትዮጵያ ድንበሮች አዋሳኝ ሃላፊ ኡቤዳ ኑር ኢሴን ጨምሮ የቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች መገደላቸው የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም