በመዲናዋ የተከናወኑ ሰው ተኮር የልማት ስራዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ትምህርት የሰጡ ናቸው-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

363

ነሐሴ 13 ቀን 2014(ኢዜአ) በመዲናዋ የተከናወኑ ሰው ተኮር የልማት ስራዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ትምህርት የሰጡ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ፡፡

ከንቲባዋ በአዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በ60 ቀናት ሰው ተኮር የልማት ስራዎች የተከናወኑ 105 ፕሮጀክቶችን መርቀው ከፍተዋል፡፡

ፕሮጀክቶቹ በመንግስትና ባለሃብቶች የጋራ ጥረት የተገነቡ ሲሆኑ፤ ከተመረቁት መካከል የምገባ ማዕከላት፣ የሸገር ዳቦ ማከፋፈያዎች፣ የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት መስጫ ቢሮዎች፣ወጣት ማዕከላት እንዲሁም የትምህርት ቤቶችና ጤና ጣቢያ ማስፋፊያ ግንባታዎች ይገኙበታል፡፡

በተጨማሪ ከንቲባዋ በኦቪድ ግሩፕ የተገነባውን ባለ 11 ወለል የመኖሪያ ህንጻ የመረቁ ሲሆን፤ ለግንባታው የወጣውን 50 ሚሊዮን ብር ወጪ ሙሉ በሙሉ በአቢሲኒያ ባንክ መሸፈኑ ተገልጿል፡፡

የመኖሪያ ቤት ግንባታው ከ50 በላይ የሚሆኑ ቤተሰቦችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም የተገለጸ ሲሆን የከተማውን ገጽታ የሚያጎሉ መንገዶች፣አካፋዮችና አደባባዮችን የማስዋብ ስራዎችም እንዲሁ ተመርቀዋል።

ከንቲባዋ በዚሁ ጊዜ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተጠናቀቁት ፕሮጀክቶች የስራ ባህላችን እየተቀየረ መሆኑን አመላካች ነው ብለዋል።

የከተማ አስተዳደሩ በመዲናዋ ያለውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለማቃለል ከባለሃብቶች ጋር በጋራ እየሰራ እንደሚገኝም አብራርተዋል፡፡

ዛሬ የተመረቀው ባለ11 ወለል መኖሪያ ህንጻ በዚሁ መሰረት የተገነባ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡

የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዘመኑ ደሳለኝ በበኩላቸው በዘንድሮው ዓመት በክፍለ ከተማው በሰው ተኮር ልማት ስራዎች 280 ቤት ግንባታ እንዲሁም የ931 ቤቶች እድሳት መከናወኑን ተናግረዋል።

በ60 ቀናት ሰው ተኮር ልማት እንቅስቃሴ የተገኘው ውጤት የስራ ባህላችን ከተሻሻለ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብልጽግናን ማረጋገጥ እንደሚቻል ልምድ የተገኘበት ነው ሲሉም አክለዋል።

ዛሬ ለምረቃት በበቁት ፕሮጀክቶች አማካኝነት ከ 5 ሺህ 800 በላይ ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩንም ገልጸዋል።

ባለ11 ወለል ቤቶች ግንባታ ያካሄደው የኦቪድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዮናስ ታደሰ በበኩላቸው የህንጻው ግንባታ የተጠናቀቀው 69 ቀናት መሆኑን አስረድተው ለዚህ ደግሞ አዲስ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ መዋሉንም አመልክተዋል።

ከንቲባዋ ዛሬ ከተመረቁት ፕሮጀክቶች መካከል የንግድና መስሪያ ቦታዎችን ለተደራጁ ዜጎች እንዲሁም የመኖሪያ ቤቶችን ለአካል ጉዳተኞችና እጣ ለወጣላቸው ዜጎች አስረክበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም