በጉጂ ዞን 171 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እየተገነቡ ናቸው-- ጽህፈት ቤቱ

165

ነገሌ ነሀሴ 13/2014 (ኢዜአ) በጉጂ ዞን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትን ተደራሽ ለማድረግ 171 ትምህርት ቤቶች በግንባታ ላይ መሆናቸውን የዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

በጽህፈት ቤቱ የትምህርት ማሻሻያ ቡድን መሪ አቶ ማቲዎስ ጎበና ለኢዜአ እንደገለጹት በግንባታ ላይ ያሉት ትምህርት ቤቶቹ ከ680 በላይ የመማሪያ ክፍል ያላቸው ናቸው፡፡

የዞኑ ህዝብ ለመጀመሪያ  ደረጃ  ትምህርት  ቤቶች   ግንባታ   ከ189 ሺህ ብር  በላይ የሚገመት ነጻ የጉልበት ተሳትፎ በማድረጉን ተናግረዋል፡፡

ለ በግንባታ ስራው ላይ በመሳተፍ  ካለው 497 ሺህ  ህዝብ  ውስጥ ግማሽ  ያህሉ  ሴቶች እንደሆኑ አመልክተዋል፡፡

በዞኑ 14 ወረዳዎች የተጀመሩት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የግንባታ ስራ ሂደት አሁን ላይ ከ20 እስከ 60 በመቶ መድረሱንም ገልጸዋል፡፡

ትምህርት ቤቶቹ ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው በአዲሱ አመት አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ ከ20 ሺህ 500 በላይ  ተማሪዎችን የመቀበል አቅም እንደሚኖራቸው ተናግረዋል፡፡

በአዲሱ ዓመት 288 ሚሊዮን ብር በሚገመት የህዝብ ተሳትፎ ተጨማሪ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት በእቅድ መያዙን ጠቁመዋል፡፡

በዞኑ ሻኪሶ ወረዳ የሁዴይ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ቡቸና በለኮ በሰጡት አስተያየት ትምህርትን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ በመንግስት የተጀመረውን ጥረት እየደገፉ ናቸው፡፡

ከአካባቢያቸው ነዋሪዎች ጋር በመተባበር የጀመሩትን የግንባታ ስራ ከአዲስ ዓመት በፊት ለመጨረስ እየተረባረቡ መሆኑን በመጥቀስ፡፡

"ልጆቻችንን ለማስተማር ለግል ትምህርት ቤት የሚከፈል ወጭን የሚያስቀር በመሆኑ ሁላችንም ትምህርት ቤቶቹን  በሙሉ ፈቃደኝነት ለመስራት አነሳስቶናል" ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የተማረ አምራች ሃይል በመፍጠር ከድህነትና ኋላቀርነት ለመላቀቅ የመጀመሪያው ተግባር የትምህርት ተቋማት ተደራሽ ማድረግ ወሳኝ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በወረዳው የበንቲ አርባ ትምህርት ቤት መምህር ፍቃዱ ደበሶ ናቸው።

ባደጉት ሀገራት ቴክኖሎጂዎችን በመፍጠርና በመጠቀም ህዝቡን ተጠቃሚ በማድረግ የደረሱበትን ደረጃ ለመቀላቀል የሚቻለው የትምህርት ተቋማትን የመገንባት ስራን ለመንግስት ብቻ  በመተው  አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

"ህጻናትን በበቂ እውቀት በማነጽ ለከፍተኛ ደረጃ ለማድረስ መሰረት የሚጥሉ በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መሆኑን ወላጆች ሊገነዘቡ ይገባል" ሲሉም  ጠቅሰዋል፡፡

የሚፈለገውን  አላማ ለማሳካት ደግሞ ለትምህርት ጥራት መጠበቅ አስፈላጊ የሆነውን የተማሪ መምህር ጥምርታ ችግር ማሻሻል እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

"በግል ፍላጎትና ተነሳሽነት በግንባታ ስራው ላይ እየተሳተፍኩ ያለሁት ይሄንን ጥቅምና ጉዳት ስላወቅኩ በመሆኑ ወደፊትም ይህንንው አጠናክሬ እቀጥላለሁ" ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም