የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በበጀት ዓመቱ ከ30 ኩንታል በላይ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ለማቅረብ ማቀዱን ገለጸ

229

አሶሳ ነሐሴ 13/2014(ኢዜአ) በተያዘው በጀት ዓመት ከ30 ኩንታል በላይ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ለማስገባት ማቀዱን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማዕድን ሃብት ልማት ኤጀንሲ አስታወቀ።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ናስር መሃመድ ለኢዜአ እንዳስታወቁት ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሚገኙ ማዕድናት መካከል የደለል እና ጽንስ ወርቅ ዋነኛው ነው።

ሃብቱ የአካባቢውን ማህበረሰብ ህይወት ከመቀየር ባለፈ ለሀገር ኢኮኖሚ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ኤጀንሲው በ2015 በጀት ዓመት ልዩ ትኩረት መስጠቱን ገልጸዋል።

በህጋዊ መንገድ ተደራጅተው ለሚሰሩ ከ100 በላይ ባህላዊ ወርቅ አምራች ማህበራት 13 የወርቅ ድንጋይ መፍጫ ማሽኖች እንደሚቀርቡላቸው ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ ከ30 ኩንታል በላይ ወርቅ ከክልሉ ወደ ብሔራዊ ባንክ ለማስገባት ከባለድርሻ አካላት ጋር የተናበበ እቅድ መዘጋጀቱንም አቶ ናስር ገልጸዋል።

እንደዳይሬክተሩ ገለጻ ወርቁ የሚመረተው በክልሉ ሦስት ዞኖች ሲሆን አብዛኛው በተደራጁ ግለሰቦች በባህላዊ መንገድ እና በልዩ አነስተኛ ማህበራት ነው።

በሌላ በኩል በክልሉ ሦስት ትልልቅ ወርቅ አምራች ካምፓኒዎች ፍቃድ ከወሰዱ ረጅም ጊዜያት የተቆጠረ ቢሆንም እስካሁን ማምረት የጀመረው አንድ ካምፓኒ ብቻ ነው ብለዋል።

ማምረት የጀመረው ካምፓኒም ቢሆን ከያዘው መሬት እና ከገባው ውል አንጻር እያመረተ ያለው የወርቅ መጠን እጅግ አነስተኛ መሆኑን ገልጸው ካምፓኒዎቹ በሙሉ አቅም እንዲያመርቱ ከፌደራል መንግስት ጋር በመቀናጀት ጥረቶች መጀመራቸውንም አቶ ናስር አመልክተዋል።

የጥቁር ገበያ ወርቅ ሽያጭ የተፈጥሮ ሃብቱ ዋነኛ ፈተና እንደሆነ አንስተውም "ጥቁር ገበያውን ለማስቆም በክልሉ መንግስት የሚመራ የተጠናከረ ግብረሃይል ተቋቁሟል" ብለዋል።

ግብረሃይሉ በህገወጥ የወርቅ አዘዋዋሪዎች ላይ የማያዳግም እርምጃ እንዲወስድ አቅጣጫ መቀመጡንም ዋና ዳይሬክተሩ የተናገሩት።

ወርቅ የሃገር ኢኮኖሚን ከሚደጎሙ ሃብቶች አንዱና ዋነኛው እንደሆነ ግንዛቤ ለመፍጠር ስራዎች እንደሚሰሩም ገልጸዋል።

በተለይ ከባህላዊ አምራቾች እና ከማህበረሰቡ ጋር የጀመርናቸው ሰፋፊ ህዝባዊ የውይይት መድረኮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

በባህላዊ ወርቅ ማምረት ሥራ የተሠማሩት አቶ አዩብ አለመሃዲ በበኩላቸው፣ "በባህላዊ ወርቅ ማምረት ሥራ የተሰማሩ የወጣቶች ማህበራት ጠንካራ አደረጃጀት እንዲኖራቸው በማድረግና የቁጠባ ባህላቸውን በማሳደግ ወደተሻለ ኢንቨስትመንት የሚሸጋገሩበትን መድረክ መፍጠር ይገባል" ብለዋል።

ሃብቱ በሚገኝበት አካባቢ ሠላም በዘላቂነት እንዲረጋገጥ መንግስት ህብረተሰቡን በማስተባበር በትኩረት እንዲሰራ ጠይቀዋል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በ2014 በጀት ዓመት በባህላዊ እና በልዩ አነስተኛ ማህበራት የተመረተ ከ23 ኩንታል በላይ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ መቅረቡ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም