በዞኑ ከ177 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች መሸፈን ተችሏል---ጽህፈት ቤቱ

142

ግምቢ፣ ነሐሴ 13/2014 (ኢዜአ) በቄሌም ወለጋ ዞን በመኸር አዝመራ ከ177 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች መሸፈኑን የዞኑ ግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የዞን አርሶ አደሮች በግብርና ባለሙያዎች በመታገዝ የእርሻ ስራቸውን እያካሄዱ እንደሚገኙ ተገልጿል።

በዞኑ የዳሌ ሰዲ ወረዳ አርሶ አደር ወርቅነህ ባይሳ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም አንድ ሔክታር ማሳቸውን በቦቆሎና ስንዴ ዘር መሸፈናቸውን ተናግረዋል፡፡

የግብርና ባለሙያዎች ድጋፍና ክትትል እያደረጉላቸው መሆኑን የገለጹት አርሶ አደሩ ዘንድሮ ካለሙት  ሰብል ከ35 እስከ 40 ኩንታል ምርት ለማግኘት አቅደው እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችን በወቅቱ ገዝተው በመጠቀምና በባለሙያ ምክር በመታገዝ የእርሻ መሬታቸውን በስንዴ ዘር መሸፈናቸውን የተናገሩት ደግሞ የጅማ ሆሮ ወረዳ አርሶ አደር ሁንዴ ግርማ ናቸው።

እየዘነበ ያለው የክረምት ዝናብ ለመኸር አዝመራ አመቺ በመሆኑ የተሻለ ምርት ለማግኘት ለሰብሉ የአረምና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ክትትሎችን እያደረጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

የዞኑ ግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ኦልብራት ሁንዴሳ ለኢዜአ እንደገለፁት በ2014/15 ምርት ዘመን በዞኑ በዘር ለመሸፈን የታቀደው 177ሺህ 262 ሄክታር መሬት ሙሉ በሙሉ በዘር ተሸፍኗል ነው ያሉት።

ለዚህም 600 ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮና 70ሺህ ኩንታል የፋብሪካ ማዳበሪያ ጥቅም ላይ መዋሉን ተናግረዋል።

በዞኑ በአጠቃለይ በዘር ከተሸፈነው መሬት ላይ 6 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል፡፡

ባለፈው የምርት ዘመን 6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ምርት መሰብሰቡን የገለጹት ሃላፊው በተያዘው ምርት ዘመን  በ300 ሺህ ኩንታል ብልጫ ያለው ምርት ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ ኦልብራት እንደገለጹት በዞኑ በስፋት ከሚመረቱ ሰብሎች መካከል የበቆሎ፣ ባቄላ ፣ ስንዴና የገብስ ሰብሎች ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

በምርት ዘመኑ በዘር ከተሸፈነው 177 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት ውስጥ 130 ሺህ ሔክታሩ በኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴ የለማ መሆኑም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም