አሸባሪው ህወሃት በደቡብ ወሎ ጉዳት ያደረሰባቸው መኖሪያ ቤቶችን መልሶ የመገንባት ስራ ተጀመረ

106

ደሴ ፤ ነሐሴ 13/2014 አሸባሪው ህወሓት በደቡብ ወሎ ዞን ወረራ በፈጸመበት ወቅት ጉዳት ያደረሰባቸው ከ2 ሺህ 600 በላይ መኖሪያ ቤቶችን የመልሶ ግንባታ ስራ መጀመሩን የዞኑ ዋና አስተዳደር አስታወቁ።

ዋና አስተዳዳሪው አቶ አብዱ ሁሴን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስ በአማራና በአፋር ክልሎች በፈጸመው ወረራ የፈጸመው ግፍ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ አልፏል፡፡

ንጹሃንን በግፍ በጅምላ ከመጨፍጨፍ ባለፈ ማህበራዊ ተቋማትን ጭምር በማውደምና በመዝረፍ  ለህዝብ ያለውን ጥላቻ በተግባር አረጋግጧል፡፡

በደቡብ ወሎ ዞንም በርካታ ውድመት ቢያደርስም መንግስት ህብረተሰቡን፣ የተለያዩ ድርጅቶችንና ተቋማትን በማስተባበር በሽብር ቡድኑ የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ ከ2 ሺህ 600 የሚበልጡ መኖሪያ ቤቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ጠቁመው፤ ከተያዘው ወር መግቢያ ጀምሮ ቤቶችን  የመልሶ ግንባታ ስራ መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡

ጉዳት ከደረሰባቸውም  617 ቤቶች  ከእነ ንብረታቸው ሙሉ በሙሉ  መውደማቸውን የጠቀሱት ዋና አስተዳዳሪው፤ ቀሪዎች እስከ 90 በመቶ የወደሙ ናቸው ብለዋል፡፡

ቤቶችን መንግስት ባለሃብቶችን፣ ድርጅቶችንና ህብረተሰቡን በማስተባበር በ40 ሚሊዮን ብር መልሶ ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን  አመልክተዋል።

የቤቶቹ መልሶ ግንባታም በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ተገንብተው እንዲጠናቀቁ ጥብቅ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በአሸባሪው ጉዳት የደረሰባቸው መኖሪያ ቤቶችን በመረዳዳት መልሶ ለመገንባት የሚደረገው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የዞኑ  አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ይመር ናቸው።

ቤታቸው የወደመባቸው ዜጎች በክረምቱ ዝናብ እየተቸገሩ በመሆኑ በፍጥነት ተገንብተው ችግሮቻቸውን ለመፍታት በየደረጃው ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለአንድ ቤት 56 የቤት ክዳን ቆርቆሮና ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶች መዘጋጀታቸውን ጠቁመው፤ ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እየሰራን ይገኛል ብለዋል።

ለቤት መስሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ ካደረጉ ባለሃብቶች መካከል አቶ ነጋ መሃመድ ፤ የወሎ ባለሃብቶችን በማስተባበር ከአንድ ሺህ 300 በላይ የቤት ክዳን ቆርቆሮ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።

ሌሎች ተቋማትም መልሰው እንዲቋቋሙ ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ዜጎችም በዘላቂነት እንዲቋቋሙ ከመንግስ ጋር በቅንጅት እንሰራለን የድርሻችንንም እንወጣለን ብለዋል፡፡

አሸባሪው ህወሓት ቤታቸውን ሙሉ በሙሉ ከማውደሙ ባለፈ ላም ሽጠው ያስቀመጡትን 92 ሺህ ብር እንደዘረፋቸው የተናገሩት በተውለደሬ ወረዳ የ07 ቀበሌ አርሶ አደር ይማም መሃመድ ናቸው።

ሙሉ ንብረቴ በመዘረፉና በመውደሙ ለችግር ተጋልጨ ነበር፤ አሁን መንግስት ቤቴን መልሶ እየገነባልኝ በመሆኑ ተደስቻለሁ  ብለዋል አርሶ አደሩ፡፡

 የዚሁ ቀበሌ አርሶ አደር ሞሚና አሊ ፤ አሸባሪው ህወሓት የሰው ልጅ የማይፈጽመውን ግፍና መከራ ቢፈጽምብንም በወገኖቻችንና መንግስት ብርታት መልሰን እየተቋቋምን ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የወደመባቸውን  ቤታቸውን መንግስት ድጋፍ ሰጪዎችን  አስተባብሮ መልሶ እየገነባላቸው በመሆኑ መደሰታቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም