የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ከባህል ትውውቅ ባሻገር የሕዝቦችን ወንድማማችነት በሚያጠናክር መልኩ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው

160

ነሐሴ 13/2014 / ኢዜአ/ ለ17ኛ ጊዜ የሚከበረውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ከባህል ትውውቅ ባሻገር የሕዝቦችን ወንድማማችነትን በሚያጠናክር መልኩ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ተናግረዋል።

በኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነት በሲዳማ ክልል አስተናጋጅነት ህዳር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ለ17ኛ ጊዜ የሚከበረውን የኢትዮጵያ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን አስመልክቶ ውይይት ተካሂዷል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ እና የአብይ ኮሚቴ ሰብሳቢ አገኘሁ ተሻገር፣ የክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤዎች እና ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ አካላት በውይይቱ ላይ ተገኝተዋል።

በውይይቱም የ17ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል አከባበር ረቂቅ መሪ ዕቅድ ቀርቧል።

በዓሉ “ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት ለዘላቂ ሰላማችን በሚል መሪ ቃል ለማክበር መታቀዱን ረቂቅ እቅድ በቀረበበት ወቅት ተጠቅሷል።

በዚህ ወቅት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ቀኑ ከዚህ በፊት ሲከበር የሚስተዋሉ ውስንነቶችን በማስቀረት የሚከበር ይሆናል ብለዋል።

ለ17ኛ ጊዜ በሲዳማ ክልል ሀዋሳ ከተማ የሚከበረው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ከባህል ትውውቅ ባሻገር የሕዝቦችን ወንድማማችነትን በማጠናከር መልኩ እንዲከበር  ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ለ17ኛ ጊዜ የሚከበረው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የተሻለና በልዩ ሁኔታ ማክበር እንዲቻል ካለፉት በዓላት ተሞክሮ ለመውሰድ የዳሰሳ ጥናት መደረጉን አፈ-ጉባኤው ገልጸዋል።

ለዚህም ከፌደራል እስከ ክልል ድረስ ኮሚቴ ተዋቅሮ የቅደመ ዝግጅት ሥራ እየተሰራ ነውም ብለዋል።

በዓሉም የእርስ በርስ ትውውቅን በማጠናከር የሕገ-መንግሥት እና የፌደራል ሥርዓት አስተምህሮ ሥራዎች ላይ ውይይቶች በማድረግ እንደሚከበር ጠቅሰዋል።

አፈ-ጉባኤው በዓሉ የሕዝቦች አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ እንዲከበር ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሚያዝያ 21 ቀን 1998 ባካሄደው 2ኛው መደበኛ ጉባኤ የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት የፀደቀበት ሕዳር 29 ቀን የኢትዮጵያ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ሆኖ እንዲከበር መወሰኑን እና እስካሁንም እየተከበረ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም