ከ430 ሚሊየን ብር በላይ የኢንቨስትመንት ካፒታል ያስመዘገቡ ሦስት የአገር ውስጥ ኩባንያዎች የውል ስምምነት ፈረሙ

146

ነሐሴ 13/2014 / ኢዜአ/ ከ430 ሚሊየን ብር በላይ የኢንቨስትመንት ካፒታል ሦስት የአገር ውስጥ ኩባንያዎች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች ለመሰማራት ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር የውል ስምምነት ተፈራረሙ።

የውል ስምምነቱን የፈረሙት ‘አፊያን’ የጨርቃጨርቅና አልባሳት ማምረቻ፣ ‘አሊያኪም’ የምግብ ዘይት ፋብሪካና ‘ዶሜን አልሙኒየም ኮምፖሲት ፓኔል’ የተሰኙ ናቸው።

የውል ስምምነቱን የፈረሙት የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሳንዶካን ደበበ ከኩባንያዎቹ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ነው።

ስምምነቱን አስመልክቶ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሳንዶካን እንደገለጹት መንግሥት አቅም ያላቸው የአገር ውስጥ ባለሃብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ተሰማርተው እንዲሰሩ በትኩረት እየሰራ ነው።

በተለይም የአገር ውስጥ ባለሃብቶችን ለማበረታታት በተደረገው የአሰራር ማሻሻያ ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ አራት ባለሃብቶች በፓርኮቹ ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች እንዲሰማሩ የማግባባት ሥራ ተሰርቷል ብለዋል።

በዛሬው ዕለትም ከአራቱ ድርጅቶች ውስጥ ሦስቱ አስፈላጊውን መስፈርቶች ሙሉ በሙሉ ያሟሉ በመሆኑ ወደ ሥራ ለመግባት የሚያስችላቸውን የውል ስምምነት መፈረም አስፈልጓል ነው ያሉት።

ስምምነቱ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለባለሃብቱ ምቹ የሥራ ሁኔታን በመፍጠር አገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንድታገኝ ያግዛል።

በተጨማሪም ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል ከመፍጠር ባሻገር በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የተለያዩ ምርቶችን ማምረትና ከአገር ውስጥ አልፎ ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንደሚቻል የሚያሳይ ነውም ብለዋል።

ዛሬ የውል ስምምነት የፈረሙት ድርጅቶች የምርቶቻቸውን ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃን ያሟሉና ለዚህም የብቃት ማረጋገጫ ያላቸው መሆኑንም አክለዋል።

በተጨማሪም  ኩባንያዎቹ በአጠቃላይ ከ430 ሚሊየን ብር በላይ ኢንቨስትመንት በማስመዝገብ ዘርፉን እንደተቀላቀሉ አብራርተዋል።

የድርጅቶቹ የሥራ ኃላፊዎችና ተወካዮች በበኩላቸው፤ ኮርፖሬሽኑ ወደ ዘርፉ እንዲቀላቀሉ በግብዓትና መሰል ጉዳዮች ድጋፍ ሲያደርግ እንደነበር ይገልጻሉ።

በፓርኮቹ ውስጥ የተሰማሩበትን ዘርፍ በማሳደግ ጥራቱን የጠበቀ ምርት ለማምረት በቁርጠኝነት እንደሚሰሩም አክለዋል።

የ’አፊያን’ የጨርቃጨርቅና አልባሳት ማምረቻ ዋና ሥራ አስኪያጅ አበራ አህመድ ኩባንያቸው በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ከ6 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ መሬት መረከቡን ተናግረዋል።

ኩባንያው የጨርቃጨርቅና አልባሳት ምርትን ለውጭ ገበያ ማቅረብን ዓላማው አድርጎ መቋቋሙን ገልጸው፤ ለዚህም ከ239 ሚሊየን ብር በላይ ኢንቨስት ማድረጉን ገልጸዋል።

በዚህም ለ250 ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር መታቀዱን ነው የጠቆሙት ዋና ሥራ አስኪያጁ።

 ከአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ 5 ሺህ 500 ካሬ ሜትር መሬት መረከቡን በአልሙኒየም ውጤቶች ምርት ላይ የተሰማራው ድርጅት የ’ዶሜን አልሙኒየም ኮምፖሲት ፓኔል’ ተወካይ ስምኦን ገብረመስቀል ተናግረዋል።

ለዚህም ከ65 ሚሊየን ብር በላይ ኢንቨስት መደረጉንም እንዲሁ

ድርጅቱ ለ60 ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ያቀደ ሲሆን ምርቱን ሙሉ ለሙሉ ለአገር ውስጥ ገበያ የሚያቀርብ ይሆናል ብለዋል።

በተመሳሳይ ‘አሊያኪም’ የምግብ ዘይት ማምረቻ ሥራ አስኪያጅ ሳምሶን እስራኤል በበኩላቸው፤ ድርጅቱ በጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክ 3 ሺህ ካሬ ሜትር ሼድ ተረክቧል ብለዋል

የአቮካዶ የምግብ ዘይትን በስፋት ለማምረትና ተደራሽ ለማድረግ የተቋቋመው ኩባንያው ከ 125 ሚሊየን ብር በላይ ኢንቨስት እንዳደረገም ገልጸዋል።

ኩባንያው ለ210 ዜጎች የሥራ እድል የሚፈጥር ሲሆን ምርቶቹን ለዓለም አቀፉ ገበያ የማቅረብ እቅድ እንዳለውም አብራርተዋል።