የደብረ ታቦር በዓል በደብረ ታቦር ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው

120

ደብረ ታቦር ነሐሴ 13/2014 በደቡብ ጎንደር ዞን የሚገኙ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ ትውፊቶችን አልምቶ ለቱሪስት መስህብ በማዋል የአካባቢውን ህዝብ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።

የደብረ ታቦር በዓል በደብረ ታቦር ከተማ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ የፌደራልና የክልል አመራሮች በተገኙበት እየተከበረ ነው።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ይርጋ ሲሳይ በዓሉ የአካባቢውን ታሪካዊና ባህላዊ ትውፊቶች ለአገር ውስጥና ለውጭ ጎብኚዎች ለማስተዋወቅ እየተከበረ መሆኑን ገልፀዋል።

በዓሉን የአካባቢው አንዱ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የሚያግዙ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በተለይም ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተደረገ ጠንካራ እንቅስቃሴ በደብረ ታቦር ከተማ የሚከበረው የደብረ ታቦር በዓል እየደመቀ መምጣቱንና በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

በዓሉ ከቱሪስት መስህብነቱ ባለፈ የአካባቢውን ህዝብ ተጠቃሚ እንዲያደርግ ትኩረት መደረጉንም ጠቁመዋል።

“የደቡብ ጎንደር ዞን ህዝብ አንድነቱን በማስጠበቅ ከመንግስት ጎን ቆሞ ታሪክ መስራቱን ሊያስቀጥል ይገባል” ያሉት ደግሞ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ናቸው።

“አገር ለማፍረስ ዓልሞ የመጣውን አሸባሪው ህወሓት አከርካሪውን ተመቶ የተመለሰበት ቦታና ቀን ላይ በዓሉ መከበሩ ድርብ በዓል ያደርገዋል” ብለዋል።

አሸባሪውን ቡድን ለመደምሰስ በተካሄደ ትግል የዞኑ ህዝብ የሕይወት፣ የአካልና የንብረት መስዋዕትነት መክፈሉን አስታውሰው፣ በእዚህ የተገኘውን ድል በልማት በመድገም ድህነትን ማሸነፍ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የዞኑ ህዘብ ወራሪው ህወሓት እስካልጠፋ ድረስ ትጥቁን በማጥበቅና አንድነቱን በማጠናከር አገር ለማፅናት ከመንግስት ጎን እንዲቆም ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።

“ለዚህም በአንድ እጁ ጦር እና ጋሻ የሚይዝ፤ በሌላው እጁ ደግሞ ልማትን የሚያፋጥን ህዝብ መሆን ይኖርበታል” ሲሉ ነው ያመለከቱት።

በበዓሉ ላይ በሕፃናት፣ ወጣቶች እና ሴቶች የሆያ ሆዬ፣ የአሸንድዬና ሌሎች በዓሉን የሚያስታውሱ ዝግጅቶች የቀረቡ ሲሆን ከክልልና ከፌደራል የመጡ እንግዶችም ታድመዋል።