ዩኒቨርሲቲው በሥራ እድል ፈጠራና በሌሎች መስኮች ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ ገለጸ

94

ደሴ ነሐሴ 13/2014(ኢዜአ) ወሎ ዩኒቨርሲቲ በሥራ እድል ፈጠራና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ በሚያደርጉ መስኮች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ፋሪስ ኃይሉ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ተቋሙ ከመደበኛ የመማር ማስተማር ሥራው ጎን ለጎን የአካባቢውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ ነው።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ዩኒቨርሲቲው በደቡብ ወሎ ዞን፣ በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን እና ደሴ ከተማ አስተዳደር ከ10 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጭ የማህበረሰብ አገልግሎት ሥራዎችን ማከናወኑን አስረድተዋል።

“ከተሰሩት ሥራዎች መካከል የአቅም ግንባታ ስልጠና፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የክረምት ጎርፍ ቅደመ መከላከል፣ የዘር አቅርቦት፣ የተፈናቀሉ ወገኖችን ማገዝ እንዲሁም ተቋማትን መልሶ ማቋቋም ይገኙበታል” ብለዋል።

በተለይ በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ በአርሶ አደሮች ማሳ ላይ ይከሰት የነበረውን ጎርፍና የውሃ ማቆር ቀድሞ በመከላከል የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራት ፋይዳቸው ከፍ ያለ መሆኑን ዶክተር ፋሪስ ገልጸዋል።

በ2 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር መሬት ላይ የውሃ መፋሰሻ ቦይ እና አፈር የማጠንፈፍ ተግባር መከናወኑን የገለጹት።

“በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ተግባሩን በማጠናከር ህብረተሰቡን በተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ ነው” ብለዋል።

በደቡብ ወሎ ዞን የቃሉ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሙህዲን አህመድ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው መንግስት ተደራሽ ባልሆነባቸው አካባቢዎች ልማት በማካሄድ ህብረተሰቡን በተጨባጭ እያገዘ መሆኑን ተናግረዋል።

በወረዳው በጎርፍ ምክንያት ከምርት ውጭ የነበረ ከ100 ሄክታር በላይ መሬት ላይ የጎርፍ መከላከያ ሥራ በመስራት መሬቱ በአሁኑ ወቅት በሰብል እንዲሸፈን ማድረጉንም በማሳያነት ጠቅሰዋል።

“ከግማሽ ሄክታር የሚበልጥ ማሳዬ ከቦርከና ወንዝ ሰብሮ በሚመጣና ከተራሮች በሚወርድ ጎርፍ እየተጥለቀለቀ ላለፉት 3 ዓመታት ምርት ማግኘት ተቸግሬ ነበር” ያሉት ደግሞ በቃሉ ወረዳ የቀበሌ 033 ነዋሪ አርሶ አደር ደምስ መሃመድ ናቸው።

ጎርፉ ከማሳቸው ባለፈ መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ስለሚገባ ይፈናቀሉ እንደነበረ አስታውሰው፣ ዘንድሮ በወሎ ዩኒቨርሲቲ በተሰራላቸው የጎርፍ ቅደመ መከላከል ሥራ ማሳቸውን በማሽላ፣ በቆሎና ሌሎች ሰብሎች ለማልማት መቻላቸውን ገልጸዋል።

ወሎ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የትምህርት መርሃግብሮች ከ26 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ ከዩኒቨርስቲው የተገኘው መረጃ ያሳያል።