በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ አንድ ወር ብቻ 8 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ ተችሏል- የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ

175

ነሃሴ 13/2014/ኢዜአ/ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ በተያዘው በጀት ዐመት የመጀመሪያ ወር 8 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ፡፡

ቢሮው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት አፈፃፀምና በ2015 በጀት ዓመት እቅድ ላይ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ውይይት እያካሄደ ነው።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ተፈራ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ቢሮው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 48 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 55 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ የእቅዱን 115 በመቶ ማሳካት ችሏል።

የእቅድ አፈፃፀሙ ከ2013 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ31 በመቶ እድገት ያሳየ መሆኑንም ገልፀዋል።

ቢሮው ተቋማዊ አቅምን በማሳደግ፣ የአገልግሎት አሰጣጡን ምቹ በማድረግ፣ የህግ ተገዢነት ስራዎችን ማጠናከርን ጨምሮ በአምስት የትኩረት መስኮች ላይ ያከናወናቸው ተግባራት ለአፈፃፀሙ ውጤታማነት አስተዋፅኦ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ቢሮው በ2015 በጀት ዓመት 70 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ማቀዱን ገልፀው፤ ከዚህም ውስጥ 30 ቢሊዮኑን ከሐምሌ 1  ቀን 2014 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2015 ዓ.ም ባለው ወቅት ለመሰብሰብ አቅዶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

እቅዱን ለማሳካት የትኩረት መስኮች በተጠናከረ መልኩ እንደሚተገበሩም አብራርተዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ወር ብቻ 8 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡንና አፈጻጸሙም  107 በመቶ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ደግሞ የ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር እድገት ያሳየ መሆኑን አስረድተዋል።

በአዲስ አበባ በአጠቃላይ 438 ሺህ ግብር ከፋዮች ያሉ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ 323 ሺህ ያህሉ ደረጃ "ሐ" ግብር ከፋዮች መሆናቸውን ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም