የሳይንስና ኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ አውደ ርዕይ በባህርዳር ከተማ ተከፈተ

485

ነሐሴ 13 2014(ኢዜአ) የሳይንስና ኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ አውደ ርዕይ እንዲሁም የፓናል ውይይት በባህርዳር ከተማ ተከፈተ።

አውደ ርዕዩ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ድጋፍ በተቋቋመው የባህርዳር የሳይንስ ካፌ ለሁለት ቀናት እንደሚቆይ ተነግሯል።

አውደ ርዕዩን የከፈቱት የኢኖቬሽንና ቴከኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ በቴክኖሎጂና በኢኖቬሽን ስራንና ሀብትን ለመፍጠር የምትመች ሀገር የመገንባት ርዕይ በመሰነቅ እየተሰራ ነው ብለዋል።

“የሀገራችንን የዲጂታል ኢኮኖሚ የሚገነባበትን፤ ከባቢያዊ ስርዓት መፍጠር፣ የቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪ ልማት ተወዳዳሪነት ለማሳደግ የሚያስችል አቅም መገንባት እና ኢኖቬሽን፣ ቴክኖሎጂ እና ምርምር ለስራና ሀብት ፈጠራ አበርክቶ እንዲኖራቸው የማድረግ ተልዕኮን ለመወጣት እየሰራን እንገኛለን” ነው ያሉት።

ቴክኖሎጂዎችን በፍጥነት የመማር፣ የማላመድና የመጠቀም ሀገራዊ አቅም እንዲያድግ በኢንዱስትሪዎች፣ በከፍተኛ የምርምርና የትምህርት ተቋማት ከሚደረገው ከፍተኛ ጥረት በተጨማሪ ህብረተሰቡ በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በኢኖቬሽን ያለው ግንዛቤ ለማሳደግ በትኩረት መስራት ይገባልም ብለዋል፡፡

በሀገራችን ቀጣይነት ያለው ልማት ለማረጋገጥ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዕውቀት የተደገፉ አምራች እና ሳይንሳዊ አስተሳሰብ ያለው ዜጋ መፍጠር እጅግ መሰረታዊ ጉዳይ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ አክለውም የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ግንዛቤና ባሕል በሕብረተሰቡ ውስጥ እንዲዳብር የሳይንስ ካፌዎች ሚና ከፍተኛ ነው በማለት አመልክተዋል።

የሳይንስ ካፌዎች ከመደበኛ የትህምህርት ስርዓቱ እና ከተለመደው የማስተማር ዘይቤ በተለየ መልኩ ህብረተሰቡን በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ጉዳዮች ላይ በኢ-መደበኛ ስርዓት ግንዛቤውን እንዲያዳብር የሚሰራባቸው፣ ለወጣቱ በርካታ ሥልጠናዎች የሚሰጡባቸው፤ የስራ ፈጠራ ሃሳብ የሚጠነሰሱባቸው፣ ማንበቢያና የፈጠራ ሃሳብ የሚዳብሩበት እንዲሁም የፈጠራ ባሕል ማጎልበቻ ማዕከላት ናቸው ብለዋል።

ስለሆነም ማዕከላቱ ከትምህርት፣ ከምርምር እና ከቴክኖሎጂ ዘርፍ ተቋማት ጋር በቅርበት እንዲሰሩ ለማድረግ መሰል መድረኮች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ሲሉ አሳስበዋል።

የአማራ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን ይህን ማዕከል እንደ ሞዴል በመውሰድ በጎንደር፣ ደሴ እና ደብረብርሃን ከተሞች በማስፋት እና ሥራ በመጀመር ላይ የሚገኝ መሆኑንም አውስተው በቀጣይ እነዚህን ማዕከላት ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ አስፈላጊው ጥረት እንዲደረግ አመላክተዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዓውደ-ርዕዩ በፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች ላይ ውይይት፣ ኢግዚሂቢሽን፣ የኢኖቬሽን ሥነ-ምህዳር ስልጠና እና የፓናል ውይይቶች የሚደረጉበት መሆኑ ተመልክቷል።

በተመድ የልማት ድርጅት ድጋፍ በተዘጋጀው አውደ ርዕይ ከ2007 እስከ 2014 የተሰሩ የፈጠራ ስራዎች ቀርበው መጎብኘታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።