መንግስት ስምንት ስኳር ፋብሪካዎችን ለጨረታ አቀረበ

256

ነሐሴ 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መንግስት ኢንቨስተሮች በስኳር ፋብሪካዎች ጨረታ እንዲሳተፉ የሚጋብዝ የፍላጎት መግለጫ የጨረታ ሰነድ አቀረበ።

የግሉን ዘርፍ በስኳር ልማት ያለውን ተሳትፎና ሚና ለማሳደግ እየሰራ ያለው መንግስት የዓለም ዓቀፍና የአገር ውስጥ ኢንቨስተሮች በስኳር ፋብሪካዎች ጨረታ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርቧል።

ኦሞ ኩራዝ 1፣ ኦሞ ኩራዝ 2፣ ኦሞ ኩራዝ 3፣ ኦሞ ኩራዝ 5፣ አርጆ ዴዴሳ፣ ከሰም፣ ጣና በለስ እና ተንዳሆ ለጨረታ የቀረቡ መሆናቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ አመልክቷል።

ጨረታው እንዲወጣ የተደረገው የስኳር አምራች ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ እና የአገር ውስጥ የስኳር ፍላጎትን ለማሟላት እንደሆነ ተጠቁሟል።

የአገር ውስጥ የስኳር ፍላጎትን ሟሟላት ስኳር በማስገባት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ እንደሚያስቀርም ተገልጿል።

የስኳር ምርታማነትን ማሳደግ የሸንኮራ አገዳ አምራቾችን ገቢ በመጨመር የኑሮ ሁኔታቸውን እንደሚያሻሽልም ተነግሯል።

በተጨማሪም ለዘርፉ የሚደረገውን የመንግስት ወጪ በመቀነስ ዘርፉን ለማስፋፋትና ለማሳደግ የሚያስችል ገቢ ማመንጨት የሚያስችል ዕድል እንደሚፈጥር ተጠቁሟል።

ጨረታው ምቹ የሆነ የኢንቨስትመንት ሁኔታ እንደሚፈጥር ያመለከተው የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ለጨረታ የቀረቡት አብዛኞቹ ፋብሪካዎች አዳዲስ መሆናቸውን አመልክቷል።

ፋብሪካዎቹ መሰረተ ልማት የተሟላላቸው፣ የውሃ አቅርቦት ችግር የሌለባቸው፣ የመሬት ሃብት ያላቸው፣ ለሸንኮራ አገዳ ልማት ምቹ የአየር ሁኔታ ያላቸው እንደሆኑ ገልጿል።

ኢታኖልና የኤሌክትሪክ ሃያል ማመንጨት የሚያስችል አቅም እንዳላቸውም ጠቁሟል።

የጨረታ ሂደቱ ግልጽና የተቀላጠፈ እንዲሆን የኢትዮጵያ መንግስት ‘አርነስት ኤንድ ያንግ ኤልኤልፒ የተባለውን አማካሪ ድርጅት ድጋፍ እንዲያደርግ መምረጡን አስታውቋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም