የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በሚፈጥረው ሰው ሰራሽ ሀይቅ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የመሰማራት ፍላጎት አለን - ባለሀብቶች

217

ነሐሴ 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በሚፈጥረው ሰው ሰራሽ ሀይቅ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ኢዜአ ያነጋገራቸው ባለሀብቶች ተናገሩ።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 3ኛ ዙር የውሃ ሙሌት እና ሁለተኛው ተርባይን ሃይል ማመንጨት ስራ በስኬት መጠናቀቁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባለፈው ሳምንት ማብሰራቸው ይታወቃል።

ግድቡ ከሃይል ማመንጨት በተጨማሪ በቱሪዝም ልማትና በዓሳ ሃብት ለኢትዮጵያ ጉልህ የኢኮኖሚ ምንጭ እንደሚሆን ተናግረዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በሚፈጥረው ሰው ሰራሽ ሀይቅ 70 ደሴቶች የሚፈጠሩ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።

በመሆኑም በዚህ ውብ አካባቢ በተለይም በቱሪዝም ዘርፍ ላይ በመሰማራት ሆቴሎችና ሪዞርቶች በመገንባት ትልቅ የኢንቨስትመንት አማራጭ ማድረግ እንደሚቻል አመላክተዋል።

በዚሁ ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ ባለሀብቶች ግድቡ ሲጠናቀቅ በተለይም በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የመሰማራት ከፍተኛ ፍላጎት እንደላቸው ተናግረዋል።

በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ተሰማርተው የሚገኙት ባለሀብቱ አቶ በላይነህ ክንዴ፤ የግድቡ 3ኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ የላቀ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።

May be an image of 1 person, sitting and standing

የግድቡ ግንባታ ሲጠናቀቅ ከሚያስገኘው የሃይል ጠቀሜታ ባለፈ በሃይቁ ዳርቻዎችና በደሴቶቹ ላይ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ትልቅ ገቢ ማመንጨት ያስችላል ብለዋል።

በመሆኑም እሳቸውም ግድቡ ሲጠናቀቅ በዘርፉ ልማት የመሳተፍ ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።

የግድቡ ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ የድርሻቸውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠው በህዝቡ እየተደረገ ያለው ድጋፍ መጠናከር አለበት ብለዋል።

የዲሊኦፖል ሆቴል ስራ አስኪያጅ አቶ ግሩም በሃይሉ፤ ግድቡ ሲጠናቀቅ ትልቅ ሰው ሰራሽ ሀይቅ እና በርካታ ደሴቶቸን የሚፈጠር በመሆኑ በተለይም ለሆቴልና ቱሪዝም ጥሩ የኢኮኖሚ እድል ይዞ ስለመምጣቱ ገልጸዋል።

May be an image of 1 person, suit and indoor

በመሆኑም በዚህ ዘርፍ ወደ ፊት ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ በተለይም በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ በርካቶችን ማሳተፍ ስለሚችል ለዚሁ ልማት ሁላችንም ከወዲሁ ልንዘጋጅ ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም