ለአገራዊ ምክክሩ መሳካት የክልሉ አመራርና ህብረተሰብ ተሳትፏቸውን እንዲያጎለብቱ ተጠየቀ

135

ሀረር፣ ነሐሴ 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) የሀረሪ ክልል አመራሮችና ህብረተሰብ ለአገራዊ ምክክሩ መሳካት ተሳትፏቸውን እንዲያጎለብቱ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ጠየቀ ፡፡

አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከሐረሪ ክልል አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ የትውውቅ መድረክ አካሂዷል።

አገራዊ ምክክሩ በአገሪቱ የሚስተዋሉ አለመግባባቶችን በውይይት መፍታትን ታሳቢ ያደረገ በመሆኑ ለስኬታማነቱ አስፈላጊውን እገዛና ድጋፍ እንደሚያደርጉ የክልሉ አመራሮች አስታውቀዋል፡፡

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን አባል ኮሚሽነር መላኩ ወልደ ማርያም በመድረኩ ላይ እንደገለጹት ሁላችንም እኩል የምንኮራባት፣ ማንም ባይተዋር የማይሆንበትና እኩል ተጠቃሚ የሚሆንበትን አገር ለመፍጠር ምክክር ያስፈልጋል።

“ለአገራዊ ምክከሩ ስኬታማነት የክልሉ አመራሮችና ህብረተሰብ ተሳትፎ ወሳኝነት አለው” ብለዋል።

“አገራዊ ምክክር በአንድ አገር ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ቋንቋ፣ ሃይማኖት ፣ ወግ እና ልማድ ያላቸው ህዝቦች ሁሉን አካታች በሆነ መልኩ አገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ተመካክረው ወደ መግባባት የሚመጡበት ነው” ሲሉም አክለዋል።

ኮሚሽነር መላኩ አያይዘው “አገራዊ ምክክሩ አንዱ አሸናፊ ሌላው ተሸናፊ የሚሆንበት ሳይሆን ሁሉም የሚያሸንፍበት ነው” ብለዋል ፡፡

“ችግሮችን በሃይልና በጠመንጃ መፍታት እስከ ዛሬ መስዋእት አስከፍሎናል” ያሉት ደግሞ ኮሚሽነር አምባሳደር መሃሙድ ዲሪር ሲሆኑ አገራዊ ውይይቱ ኢትዮጵያውያንን ከገባንበት የችግር አረንቋ የሚያወጣ ነው ተብሎ ተስፋ የተጣለበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የሃረሪ ክልል ምክትል ርእሰ መስተደሰድር ወይዘሮ ሚስራ አብደላ አገራዊ ምክክሩ እያንዳንዱ ዜጋ በአገራዊ አጀንዳ ላይ የጋራ አቋም ለመያዝ የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል ፡፡

ምክክሩ ዲሞክራሲያዊ ስርአቱን በመለማመድ ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት የሚያስችል ባህል ለማዳበር የሚያግዝ ነው ያሉ ሲሆን ውይይቱ በከፍተኛ አመራሩ መጀመሩን አስገንዝበዋል ፡፡

የሃረሪ ክልል ገቢዎች ባለስልጣን ሃላፊ አቶ በቀለ ተመስገን አለመግባባታችን በዜጎች እና አገራችን ላይ ድህነት እና ውርደትን እንጂ ሌላን አይጨምርም ያሉ ሲሆን የሰሜኑ ጦርነት በርካታ የሰው ሂወትን ከመቅጠፉ ባሻገር ለከፍተኛ የኢኮኖሚ ኪሳራ የተዳረግንበት ነው አገራዊ ምክክሩ አሳታፊ በመሆነ መልኩ ሊካሄድ ይገባል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰተዋል፡፡

የክልሉ ትምርት ቢሮ ሃላፊ ሃላፊ አቶ ሙክታር ሳሊህ በበኩላቸው አገራዊ ምክክሩ በእያንዳንዱ ነገር ላይ ተወያይተን መግባባት የምንፈጥርበት ለአገር ብልፅግና ወሳኝ የሆነ አጀንዳ ነው ያሉ ሲሆን ለምክክሩ መሳካት አስፈላጊውን ድጋፍ እና እገዛ ለማድረግ ዝግጁ ነን ብለዋል ፡፡

በትውውቅ መድረኩ የኮሚሽኑ አመራሮች፣የክልሉ ከፍተኛ እና መካከለኛ ባለስልጣናት እና ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን በኮሚሽኑ የህግ ማእቀፍ እና ኮሚሽኑ የተጓዘበትን ሂደት በተመለከተ መነሻ ሀሳብ ቀርቦ ውይትት ተካሄዶበታል።