ባንኩ “ነዳጅ” የተሰኘ የክፍያ መተግበሪያን ለመጠቀም የሚያስችል ስምምነት ኤግል ላይን ሲስተም ቴክኖሎጂ ከተባለ ኩባንያ ጋር ተፈራረመ

481

ነሐሴ 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ “ነዳጅ” የተሰኘ የክፍያ መተግበሪያን ለመጠቀም የሚያስችል ስምምነት ኤግል ላይን ሲስተም ቴክኖሎጂ ከተባለ ኩባንያ ጋር ተፈራረመ።

የባንኩ የዲጂታል ባንኪንግ ምክትል ፕሬዚዳንት ዳህላክ ይገዙ እና የኤግል ላይን ሲስተም ቴክኖሎጂ ዋና ስራ አስፈጻሚ በሱፍቃድ ጌታቸው ስምምነቱን ተፈራርመዋል።

መተግበሪያው ከንግድ ባንክ ሲስተም ጋር በመገናኘት በቀላሉ የነዳጅ ግብይትን በዲጂታል መንገድ መፈፀም የሚያስችል ነው ተብሏል።

መተግበሪያው በጥሬ ገንዘብ የሚከናወነውን የነዳጅ ግብይት በዲጂታል ክፍያ ስርዓት የሚቀይር እና መንግስት ያወጣውን የነዳጅ ድጎማ ስርዓት በተሻለ መንገድ ለመተግበርና ለመቆጣጠር ያስችላል ተብሏል።

መተግበሪያው ለአሽከርካሪዎች፣ ለነዳጅ ማደያዎችና ለነዳጅ ተቆጣጣሪ የመንግስት አካላት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለውም ተገልጿል።

የባንኩ የዲጂታል ባንኪንግ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ዳህላክ ይገዙ እንዳሉት ባንኩ የክፍያ ስርዓትን ዓለም ከሚጠቀምበት የቴክኖሎጂ ደረጃ ለማድረስ እየተጋ ነው።

የክፍያ ስርዓቱን ለማዘመን በሚደረግ ጥረት ሀገር በቀል የቴክኖሎጂ ተቋማት እንዲበረታቱ ባንኩ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

ስምምነቱ የነበረውን የነዳጅ ጣቢያ የገንዘብ አከፋፈል ስርዓት ወደ አስተማማኝና ዘመናዊ የዲጂታል ክፍያ ስርዓት የሚቀይር መሆኑን ተናግረዋል።

የኤግል ላይን ሲስተም ቴክኖሎጂ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ በሱፍቃድ ጌታቸው፤ መተግበሪያው ሞተር ብስክሌት፣ መለስተኛና ከባድ ተሽከርካሪዎች ከማደያዎች ነዳጅ እንዲቀዱ ያስችላቸዋል ብለዋል።

መተግበሪያው አሽከርካሪዎች በብድር የነዳጅ ግብይት ለመፈፀም የሚያስችል ሲሆን ማንኛውም ሰው በቀላሉ ሊጠቀምበት እንደሚችልም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአጠቃላይ ከ27 ሺህ በላይ የዲጂታል ባንኪንግ ደንበኞች እንዳሉት ለማወቅ ተችሏል።