በታዳሽ ኅይል የሚሰሩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የምርት እድገትን ለማፋጠን እየተሰራ ነው- ኢንጅነር አይሻ መሀመድ

183

ነሐሴ 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) በታዳሽ ኅይል የሚሰሩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የምርት እድገትን ለማፋጠን እየተሰራ መሆኑን የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትሯ ኢንጅነር አይሻ መሀመድ ገለጹ።

የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርና ፕሪሳይስ ኮንሰልት ከተሰኘ ድርጅት ጋር በመተባበር የመስኖ ልማት የሚውሉ በፀሐይ ኅይል የሚሰሩ ቴክኖሎጂ አምራቾችን መደግፍ የሚያስችል መርሐ ግብር ይፋ አድርጓል።

የመስኖ ልማትን ለማስፋፋት ያለመው ይህ መርሐ ግብር በአማራ፣ ኦሮሚያና ሌሎችም ክልሎች ገቢራዊ እንደሚደረግ ተገልጿል።የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትሯ ኢንጅነር አይሻ መሀመድ፤ አገራዊ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ገቢራዊ እየተደረጉ ከሚገኙ ስትራቴጂዎች መካከል የመስኖ ልማት አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ሚኒስቴሩ ከትልልቅና መካከለኛ የመስኖ ፕሮጀክቶች ባሻገር የታዳሽ ኅይል ቴክኖሎጂን በመጠቀም አነስተኛ መስኖ ላይ የተሰማሩ አካላትን ማብቃት ላይ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

May be an image of 6 people, people standing and indoor

ከአምስት ሄክታር መሬት በታች ይዞታ ባላቸው የአነስተኛ ግብርና ባለይዞታ አርሶ አደሮች 40 በመቶውን አገራዊ ዓመታዊ ጥቅል ምርት ስለሚሸፍኑ ሚኒስቴሩ በትኩረት ይሰራበታል ነው ያሉት።

በዚህም ሚኒስቴሩ አነስተኛ ዋጋ ያላቸውን የውሃ እና የኅይል አማራጮች በመጠቀም የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመስኖ ልማት ስትራቴጂው መሰረትም ከከባቢ አየር ጋር ተስማሚና ውጤታማ የታዳሽ ኅይል ቴክኖሎጂዎችን በአገር ውስጥ ማምረትና በመገጣጠም አነስተኛ መስኖ ልማትን ዕውን ማድረግ ነው ብለዋል።

መርሐ ግብሩም የፀሐይ ኅይል ተጠቃሚ የውኃ ፓምፖችን ማቅረብ ብቻ ሳይሆን የፀሐይ ኅይል ቴክኖሎጂዎችን በአገር ውስጥ ገጣጥሞ በመጠቀም ለአነስተኛ መስኖ ልማት ማፋጠን መሆኑን ገልጸዋል።

መርሐ ግብሩ በአነስተኛ መስኖ ልማት የተሰማሩ አርሶ አደሮችን ተግዳሮቶች ማቃለል፣ በፀሐይ ኅይል የሚሰሩ የውሃ ፓምፖች በመጠቀም የመስኖ ስራን ለማስፋፋት የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል።

በተለይም አነስተኛ መስኖ ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮችን የሶላር ሃይል ቴክኖሎጂን በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን እንዲያሳድጉና የምግብ ዋስትን እንዲያረጋግጡ ያግዛል ብለዋል።

አሁን ላይ ከ5 ሚሊየን ሊትር በላይ ነዳጅ የሚጠቀሙ ከ200 ሺህ የሚጠጉ አነስተኛ የነዳጅ ፖምፖች ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳሉ ጠቅሰው፤ ይህ ሁኔታ የከባቢ አየር ብክለት እንደሚያስከትል ተናግረዋል።

በዚህም በነዳጅ የሚሰሩ አነስተኛ የመስኖ ቴክኖሎጂዎችን በፀሐይ ታዳሽ ኅይል በመተካት የከባቢ አየር ብክለት ቅነሳና የነዳጅ ወጭ ቁጠባን እንደሚያመጣ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በፀሐይ ታዳሽ ኅይል የሚሰሩ የአነስተኛ መስኖ ቴክኖሎጂዎችን በአገር ውስጥ መገጣጠም ከተቻለ 20 በመቶ የዉጭ ምንዛሬን እንደሚያስቀር ገልጸዋል።

የፀሐይ ኅይል የሚሰሩ ፓምፖች መገጣጠምና የመጠቀም መርሐ ግብርም ሚኒስቴሩ ዓለም ባንክና ከሌሎች ተቋማት ጋር ለሚሰራቸው ስራዎች ውጤታማነት ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

የፕሪሳይስ ኮንሰልት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሔኖክ አሰፋ በበኩላቸው በፀሐይ ኅይል የሚሰሩ የመስኖ ቴክኖሎጂዎችን በአገር ውስጥ መገጣጠማቸው በስራ ዕድል ፈጠራ ትልቅ እድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

ቴክኖሎጂዎቹ በአነስተኛ መስኖ ልማት የተሰማሩ አርሶ አደሮች ተግዳሮች ከመቅረፍ ባሻገር ለአገራዊ ቴክኖሎጂ አቅም ግንባታም ተጨማሪ እሴት እንደሚፈጥሩ ገልጸዋል።