በአዳማ ከተማ የኢንቨስትመንት መሬት ወስደው ወደ ልማት ያልገቡ 78 ድርጅቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ

123

ነሐሴ 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአዳማ ከተማ የኢንቨስትመንት መሬት ወስደው ሳያለሙ አጥረው ያስቀመጡና መሬቱን ከተረከቡበት ዓላማ ውጭ መጋዘን ገንብተው በሚያከራዩ 78 ድርጅቶች ላይ እርምጃ መውሰዱን የከተማዋ አስተዳደር ገለፀ።

በከተማዋ በኢንቨስትመንት ተቋማትና ድርጅቶች የሚስተዋሉ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት የተቋቋመ የመስተዳደሩና የባለሃብቶች የጋራ ፎረም ዓመታዊ ጉባኤ ዛሬ ተካሄዷል።

የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ እንደገለጹት፤ መስተዳደሩ 175 ሄክታር በላይ የኢንቨስመንት መሬት ለአልሚ ባለሃብቶች ዝግጁ ተደርጓል።

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከ13 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ 131 ባለሃብቶች የኢንቨስመንት ፈቃድ ተሰጥቶ አብዛኛዎቹ ወደ ልማት መግባታቸውን አመልክተዋል።

በኢንቨስመንት ዘርፍ በሚሰጠው አገልግሎት የባለሃብቱን ፍላጎት ለማርካት የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተግባራዊ መደረጉን ጠቅሰው፤ ባለሃብቱ ከአንድ ማዕከል አገልግሎት ውጭ በተናጠል ጉዳይ ለማስፈፀም ባለሙያዎች ዘንድ መሄድ እንደማያስፈልገው አስገንዝበዋል።

"አገልግሎት አሰጣጡን ከሰው ንክኪ ነፃ ለማድረግ የተዘረጋውን አሰራር በመተው በአቋራጭ ለመበልጸግ የሚሄዱ ባለሃብቶች፣ አመራሮችና ሠራተኞችን በጋራ መታገል ይገባል" ብለዋል።

በተለይ የመሬት፣ የውሃ፣ የኤሌክትሪክና የቴሌኮም አገልግሎት በአንድ ማዕከል ለመስጠት ዝግጅቱ መጠናቀቁን ጠቁመዋል።

የማሽነሪዎች ተከላ አጠናቀው መሰረተ ልማትን ጨምሮ በተለያየ ምክንያት ወደ ስራ ያልገቡ ባለሀብቶችን ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በትብብር መስራት አለብን ያሉት ከንቲባው፤ ጠንካራ የጋራ ፎረም እንዲኖር መስተዳድሩ ተገቢውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

የአዳማ ከተማ የኢንቨስመንት ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ቱራ ግዛው በበኩላቸው የኢንቨስትመንት መሬት ወስደው ሳያለሙ ለሶስተኛ ወገን ለማስተላለፍ አጥረው ያስቀመጡ 78 ድርጅቶች ላይ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል።

"መሬቱን ሸጠው በአቋራጭ ለመበልፀግ የሚንቀሳቀሱት ላይ እርምጃ ወስደናል" ያሉት ሃላፊው፤ በእርምጃው ከ100 ሄክታር መሬት በላይ ወደ መሬት ባንክ መመለሱን ተናግረዋል።

ከመስተዳደሩ ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪና ለግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ልማት በሚል መሬት ተረክበው ማከማቻ መጋዘኖችና ህንፃዎችን በመገንባት  በሚያከራዩት ላይ ፈቃድ ከመንጠቅ እስከ መሬት መቀማት ድረስ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አስታውቀዋል።

በኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሃብቶች በመሬትና በኤሌክትሪክ አቅርቦት ዙሪያ ችግሮች እንዳሉ ጠቁመዋል።

የአንድ ማዕከል አገልግሎት የነበረውን እንግልት በመቀነስ ረገድ ጥሩ ጅምር ስራዎች እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ አገልግሎቱን  በቴክኖሎጂ  ተደግፎ ሊጠናከር እንደሚገባ አመልክተዋል።

ፎረሙ ችግሮችን ለመፍታት የያዘውን ዕቅድም አድንቀዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም