መገናኛ ብዙሃን ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከር ለህዝቦች አንድነት መጎልበት የጎላ አስተዋጾ እያደረጉ ነው-ዶክተር ለገሰ ቱሉ

220

ነሐሴ 12 ቀን 2014 (ኢዜአ)የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከር ለህዝቦች አንድነት መጎልበት የጎላ አስተዋጾ እያደረጉ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ ቱሉ ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በጎንደር ከተማ ‘’ኢትዮጵያ እያሸነፈች ትሻገራለች’’ በሚል መሪ ቃል ያዘጋጀውና ሚዲያ ስለ ኢትዮጵያ የተሰኘ የፓናል ውይይት ዛሬ ተካሂዷል።

በፓናል ውይይቱ የመክፈቻ ስነ-ስርአት ላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ የገጠሟትን የህልውና አደጋዎች በህዝቧ አንድነትና ተጋድሎ እንድትሻገር በማድረግ በኩል ሚዲያው ያበረከተው አስተዋጽኦ በቀላሉ አይታይም።

የውስጥና የውጪ ጠላቶችን ሴራና የጥፋት ተግባር በማክሸፍና ኢትዮጵያ አሸናፊ እንድትሆን በማድረግ በኩል የሀገር ውስጥ ሚዲያና የማህበራዊ ሚዲያው አዎንታዊ አበርክቶ ከፍተኛ እንደነበር ተናግረዋል።

ዶክተር ለገሰ እንዳሉት የአፍራሽ ሃይሎችን ቅስቀሳና ፕሮፓጋንዳ መክቶ በመመለስ ኢትዮጵያ ሰላም እንድትሆን የግልና የመንግስት መገናኛ ብዙሀን በጋራ በመቆም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

ህብረ ብሔራዊ አንድነትንና ወንድማማችነትን በመገንባትና ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር በኩል ሚዲያዎች ሚናቸውን እንዲያጎለብቱም አሳስበዋል።

“የሚዲያና የኮሚዩኒኬሽን አውታሮች አንድ ሆነውና አንድ ላይ ቆመው ኢትዮጵያን አሻግረዋታል” ያሉት ደግሞ የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሃመድ እድሪስ ናቸው።

በፍጥነት እያደገ የመጣው የዲጂታል ሚዲያ በአግባቡ የሚመራበትን ስርአት መዘርጋት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

“ዲጂታል ሚዲያው ለህብረተሰብ አንድነትና ለብሔራዊ ጥቅም ወሳኝ ሚና መጫወት የሚችልበት አግባብ መመቻቸት አለበት” ብለዋል።

“የፓናል ውይይቱ ዋና ዓላማ እንደ ሀገር ያሉ እድሎችን ተረድተን፤ ፈተናዎችንና ተስፋዎችን አውቀን ሀገርን በማሻገር ረገድ ሚዲያዎች የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማስቻል ነው” ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጌትነት ታደሰ ናቸው።

ስለ ብሔራዊ መግባባት፣ ስለ ፍቅርና አንድነት እንዲሁም በሀገር ሉአላዊነት ላይ በመምከር ሚዲያው ምንና እንዴት ያበርክት በሚለው ላይ የፓናል ውይይቱ ትኩረት አድርጎ መዘጋጀቱንም አስረድተዋል።

እስካሁን ጎንደር ከተማን ጨምሮ በ9 ከተሞች የፎቶግራፍ አውደ ርዕይና የፓናል ውይይቶች መካሄዳቸውን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ በቀጣይ በሦስት ከተሞች መሰል መድረኮች እንደሚዘጋጁ ጠቁመዋል።

በፓናል ውይይቱ ላይ የሚዲያ ነጻነትና ተጠያቂነት፣ሚዲያና ብሔራዊ ጥቅም እንዲሁም የማህበራዊ ሚዲያ ስኬትና ተግዳሮቶች በሚሉ ርዕሶች ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

ለአንድ ቀን በተካሄደው የፓናል ውይይት ላይ የፌደራል፣ የክልል እና የጎንደር ከተማ አመራሮችን ጨምሮ የሚዲያ የሥራ ሃላፊዎችና በተለያዩ መገናኛ ብዙሀን የሚሰሩ ታዋቂና አንጋፋ ጋዜጠኞች ተሳትፈዋል።