አሸባሪው ህወሃት ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ የቅድመ ሁኔታ ዝርዝሮችን በማቅረብ የሰላም አማራጭ ሙከራዎች እንዳይሳኩ እንቅፋት እየሆነ ነው-ቢልለኔ ስዩም

ነሐሴ 12 ቀን 2014 (ኢዜአ)አሸባሪው ህወሃት ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ የቅድመ ሁኔታ ዝርዝሮችን በማቅረብ የሰላም አማራጭ ሙከራዎች እንዳይሳኩ እንቅፋት እየሆነ ነው ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታርያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ገለፁ።

ኃላፊዋ ለአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ስለ ሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም ስለሰላም እና ጸጥታ፣ ለሰሜኑ ግጭት ሰላማዊ እልባት ለመስጠት ባሉ ጥረቶች፣በሰብዓዊ ድጋፎች እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ላይ አተኩረዋል።

መንግስት ከጦርነቱ መጀመር አስቀድሞም የሰላም አማራጭን ቅድሚያ የሚሰጠው እንደነበር አስታውሰው “ህወሃት አሁንም ወደ ጦርነት ለመግባት ተደጋጋሚ ትንኮሳዎችንና ሙከራዎችን እያደረገ ነው” ብለዋል።

ለዜጎች ሁሉንም አይነት አገልግሎቶች የማቅረብና ሰላምና ጸጥታ የማረጋገጥ ቀዳሚ ተግባር የመንግስት ነው”ያሉት ሃላፊዋ አሸባሪው ህወሃት ግን የሰላም አማራጭ ሙከራዎች እንዳይሳኩና መሰረታዊ አገልግሎቶችም እንዳይጀምሩ እንቅፋት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

መንግስት በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር የሰላም ንግግር ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ደጋግሞ ማሳወቁን ገልጸው “በህወሃት የሚሰነዘሩ ስም የማጥፋት ዘመቻዎች የኢትዮጵያ መንግስት ያቀረባቸውን የሰላም አማራጮች ካለመቀበል የሚመነጩ ናቸው” ብለዋል።

በሰላም አማራጭ ዐቢይ ኮሚቴ የተዘጋጀውም ሰነድ መንግስት ግጭቱ በሰላማዊ መንገድ በሚፈታበት ሁኔታ ላይ እያደረገ ያለውን ከፍተኛ ጥረት አመላካች እንደሆነ ነው የተናገሩት።

የሰላም ውይይት ምንም አይነት ቅድመ ሁኔታ የሚያስፈልገው አይደለም ነው ያሉት።

የቴክኒከ ስራዎች እንዲሰሩና ተቋርጠዋል የተባሉ አገልግሎቶች እንዲቀጥሉ ለማስቻል የሰላም አማራጮች መኖራቸው የግድ መሆናቸውን ያሰመሩበት ፕሬስ ሴክሬቴሪዋ አገልግሎቶችን ለማስጀመር የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች መመቻቸታቸው አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም