የመቱ ካርል ሪፈራል ሆስፒታል በ59 ሚሊዮን ብር የማስፋፊያ ግንባታ እያካሄደ ነው

151

መቱ፣ ነሐሴ 12/2014 (ኢዜአ) መቱ ካርል ሪፈራል ሆስፒታል የሚሰጠው የሕክምና አገልግሎት ተደራሽነትና ጥራት ለማሳደግ በ59 ሚሊዮን ብር ወጪ የማስፋፊያ ግንባታ በማካሄድ ላይ መሆኑን አስታወቀ።

ግንባታው ከ85 በመቶ በላይ መጠናቀቁና በተያዘው በጀት ዓመት  አስፈላጊ የሕክምና መሳሪያዎችን በማሟላት ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።

የማስፋፊያ ግንባታው ሆስፒታሉ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠትና ተደራሽነት ለመጨመር የታቀደ መሆኑን የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ ዶክተር ሶለኒ በቀለ ለኢዜአ ገልፀዋል።

የማስፋፊያ ግንባታው የአስተዳደር፣ የድንገተኛ ፣ የቀዶ ጥገናና የጨቅላ ሕፃናት ሕክምናዎችን ለየብቻ ለመስጠት የሚያስችሉ 4 ሕንፃዎችን የያዘ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተለይ የድንገተኛ፣ የቀዶ ጥገናና የጨቅላ ሕፃናት ሕክምናዎችን በኮምፕሬንሲቭ ስፔሻላይዝድ ደረጃ ለማሳደግ በሚያስችል ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

የጨቅላ ሕፃናት ሕክምና እራሱን በቻለ ህንጻ ለብቻው አገልግሎት ለመስጠት እንዲያስችል ለማድረግ የታቀደ መሆኑን አመላክተዋል።

በሆስፒታሉ ዘርፈ ብዙ የቀዶ ጥገና ሕክምናዎች የሚሰጥበትን ክፍል ራሱን ወደ ቻለና ወደተሻለ ደረጃ ለማሳደግ  እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

የማስፋፊያ ግንባታው የሆስፒታሉን ደረጃ ወደ ኮምፕሬንሲቭ ስፔሻላይዝድ ደረጃ ለማሳደግ እየተከናወኑ ካሉ ተግባራት መካከል መሆኑን የገለፁት ደግሞ የኢሉባቦር ዞን ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ኢታና አስፋው ናቸው።

የመቱ ሪፈራል ካርል ሆስፒታል ከጋምቤላ እና ከደቡብ ክልሎች አዋሳኝ ዞኖች ለሚመጡ ታካሚዎች ጨምሮ ለኢሉባቦር ዞን ነዋሪዎች አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ የተደራሽነቱንና ጥራቱን ለማሳደግ ትልቅ አቅም እንደሚጨምርለት ተናግረዋል።

የሕክምና አገልግሎቱን ዘመናዊና ተደራሽ ለማድረግ በክልሉ ጤና ቢሮ በተመደበ 59 ሚሊዮን ብር ወጪ የማስፋፊያ ግንባታው እየተካሄደ መሆኑን አቶ ኢታና ገልፀዋል።

የመቱ ሪፈራል ካርል ሆስፒታልን ወደ ኮምፕሬንሲቭ ስፔሻላይዝድ ደረጃ ለማሳደግ የኤም አር አይ እና የሲቲ ስካን ምርመራና ሕክምና የሚሰጥበት ዲያግኖስቲክ ሴንተር ግንባታ ከ450 ሚሊዮን ብር በላይ ተመድቦ ወደ ስራ መገባቱን ቀደም ሲል  መዘገቡ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም