መዲናዋን ውብ ጽዱና ለኑሮ ምቹ ለማድረግ የጋራ ጥረታችን መቀጠል አለበት- ዶክተር ሂሩት ካሳው

206

ነሐሴ 12 ቀን 2014(ኢዜአ)መዲናዋን ውብ ጽዱና ለኑሮ ምቹ ለማድረግ የጋራ ጥረታችን መቀጠል አለበት ሲሉ የአዲስ አበባ የባህል፣ የኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው ተናገሩ።

በአዲስ አበባ ሁሉም ክፍለ ከተሞች ''አሻራችንን ለትውልዳችን'' በሚል መሪሃሳብ በአንድ ጀምበር 4 ሚሊዮን  ችግኝን የመትከል መርሃ ግብር ተካሒዷል።

የከተማ አስተዳደሩ  የኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው፤ በቦሌ ክፍለ ከተማ የአረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።

ዶክተር ሂሩት በመርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልእክትም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለአዲሱ ትውልድ የተሻለች አገር ለማስረከብ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም አዲስ አበባን ውብ ፣ጽዱና ለኑሮ ምቹ ለማድረግ ችግኞችን ከመትከል ጎን ለጎን የመንከባከብ ስራም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

በሁሉም አከባቢ እየተካሄደ ያለው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ኢትዮጵያ የምትታወቅበት የውሃ ማማ ታሪክ ለማስቀጠል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ነው ያሉት፡፡

''ይህም ከአገራችን አልፎ ለአህጉራችን ከፍተኛ ጥቅም ያለው፣ አርያ የሚሆን ተግባር ነው'' ብለዋል፡፡

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እየታየ ያለውን እርብርብ በሁሉም የልማት መስኮች በመድገም የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ማድረግ አለብን ነው ያሉት።

የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ አለምፀሐይ ሽፈራው፤ በክፍለ ከተማው በአራተኛው የአረንጓዴ አሸራ መርሐ ግብር ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይም የተተከሉ ችግኞችን የመጠበቅና የመንከባከብ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በመዲናዋ በመዲናዋ  15 ነጥብ 5 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል ከዕቅድ በላይ መሳካቱን የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ መግለፃቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም