የህዳሴ ግድቡ ኢትዮጵያን የማምረቻው ዘርፍ ማማ ለማድረግ ወሳኝ ነው- በኢትዮጵያ የኢንዶኔዥያ አምባሳደር

125

ነሐሴ 12 ቀን 2014(ኢዜአ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያ የማምረቻው ዘርፍ ማማ ለመሆን ቁልፍ ሚና እንደሚኖረው በኢትዮጵያ የኢንዶኔዥያ አምባሳደር አል ቡስራ ባንሱር ተናገሩ፡፡

ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ቆይታ ያደረጉት አምባሳደር ባንሱር፤ የህዳሴ ግድቡ ለኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ወሳኝ ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

“የህዳሴ ግድቡ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለጎረቤት ሀገራት ጭምር ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው አምናለሁ” ሲሉ ጨምረው ገልጸዋል።

ህዳሴ ግድቡ በሚያመነጨው ኃይል ኢትዮጵያን በኃይል አቅርቦት የበለጸገች ታላቅ ሀገር ያደርጋታል ያሉት አምባሳደሩ " በዚህም የኃይል አቅርቦት ማማ ትሆናለች ሲሉ" አመልክተዋል።

“በሚመነጨው ኃይል በመታገዝ ኢትዮጵያውያንና የጎረቤት ሀገራት ህዘቦች የራሳቸውን ኢንዱስትሪ በመመስረትና በቀላሉ በመበልጸግ የገቢ አቅማቸውንና ኢኮኖሚያቸውን ያሳድጋሉ" ነው ያሉት።

በርካቶች ኢትዮጵያን ድሃና በረሃብ የተጠቃች ሀገር አድርገው ይስሏታል፣ ነገር ግን “ዘወትር ለኢንዶኔዥያውያን ጎደኞቼ በተለይም በንግድ ስራ ላይ ለተሰማሩት የምነግራቸው፣ ኢትዮጵያ በ1977 ከነበረችበት ጋር ስትነጻጸር ፍጹም የተለየች አገር መሆኗን ነው" ብለዋል አምባሰደሩ።

አሁን ላይ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የጎረቤት ሀገራት ህዝቦች ኢኮኖሚያቸውን፣ ብልጽግናቸውን እና ኑሮአቸውን ማሻሻል መቻላቸውን አስረድተዋል።

በተመሳሳይ በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር ሮበርት ሴኪንቶንግ፤ የህንድ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ኢትዮጵያ የማምረቻው ዘርፍ መዳረሻ ለመሆን የያዘቸውን ጉጉት በሚገባ በመገንዘባቸው በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ መድበው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

“የህዳሴ ግድቡን በተመለከተ ህንድ ሶስቱ ሀገራት ማለትም ኢትዮጵያ ፣ግብጽና ሱዳን ተቀምጠው በመነጋጋር ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ ማምጣት አለባቸው የሚል ግልጽ አቋም አላት" ብለዋል

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደመቀ መኮንን ”ማንኛውም አይነት ሰው ሰራሽ ግፊቶች ቢያይሉብንም የህዳሴ ግድቡ የውሃ ሙሌት እውን መሆኑ አይቀርም፣ ግድቡ የኢትዮጵያውያን የአንድነት መንፈስና ህብረት የተንጸባረቀበት ነው” ማለታቸው ይታወሳል፡፡

ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡ ሶስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት እና የሁለተኛው ተርባይን ኃይል የማመንጨት ሙከራ በስኬት መጠናቀቁን ባሳለፍነው ሳምንት አብስራላች፡፡

በመርኃ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ”በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ የሚከናወኑ ድርድሮችና እውነተኛ ምክክሮች ከማንኛውም አማራጭ በተሻለ ፍሬያማ ውጤት ያስገኛሉ’ ማለታችው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም