የክልሉ ሴቶችን የኢኮኖሚ አቅም ለማጠናከር በተደረገው ርብርብ ከ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ቁጠባ ተሰብስቧል--ቢሮው

97

አዳማ ነሐሴ 12/2014 (ኢዜአ) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የክልሉን ሴቶች የኢኮኖሚ አቅም ለማጠናከር በተደረገው ርብርብ ከ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ቁጠባ መሰብሰቡን የኦሮሚያ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ገለፀ።

የቢሮው ምክትል ሃላፊ ሰርካለም ሰቡ ለኢዜአ እንደገለፁት የክልሉን ሴቶች ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ለማላቀቅ ሰበታ አዮ የእናቶች የቁጠባ ንቅናቄ በመፍጠር ከ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ እንዲቆጥቡ ተደርጓል።

የሰበታ አዮ የቁጠባ ንቅናቄ በየደረጃው ያሉ የሴቶች አደረጃጀቶች ፤በተለይ የሴቶች ፌዴሬሽን፣ ማህበራትና የሴቶች ሊግ አመራሮችና መላው አባላት የነበራቸው ሚና ከፍተኛ እንደነበር ጠቅሰዋል።

ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ለሚበልጡ ሴቶች ንቅናቄውን ተደራሽ ማድረግና ስለ የቁጠባ ፕሮግራሙ ግንዛቤ አግኝተው ተሳታፊ እንዲሆኑ መደረጉን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ ሴቶች በቆጠቡት ልክ የብድር አገልግሎት፣ የሙያና ክህሎት ስልጠና እንዲያገኙ መደረጉንም ገልጽው ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ የብድር አገልግሎት ማግኘታቸውን አስታውቀዋል ።

በብልጽግና ሴቶች ሊግ የኦሮሚያ የአደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊ ወይዘሮ መብራት ባጫ እንዳሉት በሴቶች ሊግ አደረጃጀት ብቻ ከ240 ሚሊዮን ብር በላይ ቁጠባ መሰብሰቡን ነው የገለፁት።

በተለይ የሴቶችን የቁጠባ ባህል ለማዳበር ከሊጉ አባላት ባለፈ መላው ሴቶች ስለ ሰበታ አዮ በቂ ዕውቀት ኖሯቸው እንዲቆጥቡ ከሲንቄ ባንክና ከተለያዩ ማይክሮ ፋይናንስ ጋር በትብብር እየተሰራ ነው ብለዋል።

በአዲሱ በጀት ዓመት "የተዛባ አመለካከትንና የአቅም ማነስና አሁንም ማነቆ ነው" ያሉት ሃላፊዋ፣  የክልሉ ሴቶች ሙሉ በሙሉ ወደ ቁጠባ ባህል ለማስገባት ይሰራል ብለዋል።

የአዳማ ከተማ ሴቶች ሊግ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ በሪራ ዑስማን በበኩላቸው የሴቶችን የቁጠባ ባህል ማዳበር ላይ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ ሰበታ አዮ የሚል የሴቶች የቁጠባ ኢንሼቲቭ በክልሉ መንግስት ተቀርጾ ተግባራዊ በመደረጉ መልካም አጋጣሚ መፍጠሩን ገልጸዋል።

በከተማዋ ንቅናቄ በመፍጠር በሰበታ አዮ ፕሮግራም በርካታ ሴቶች ወደ ቁጠባ ማዕቀፍ እንዲገቡ መደረጉን ጠቅሰው፣ በአዲሱ በጀት ዓመት በእናቶች ቁጠባ ላይ የተሻለ ስራ ለመስራት ዝግጅት እያደረገ መሆኑ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም