በደቡብ የኢትዮጵያ ክፍል ህገ ወጥ የመድኃኒት ንግድና ኮንትሮባንድ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ባለስልጣኑ አስታወቀ

165

ዲላ  ነሐሴ 12 ቀን/2014 (ኢዜአ) በደቡብ የኢትዮጵያ ክፍል ህገ ወጥ የመድኃኒት ንግድና ኮንትሮባንድ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን አስታወቀ።

ጉምሩክ ኮሚሽን በበኩሉ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት መድሀኒትን ጨምሮ በኮንትሮባንድ የገቡ ከ460 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የተለያዩ እቃዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን የደቡብ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ንማኔ ለኢዜአ እንዳሉት ጽህፈት ቤቱ በደቡብ የኢትዮጵያ ክፍል ና ሲዳማ ክልሎች እንዲሁም በኦሮሚያ 6 ዞኖችና 4 ከተማ አስተዳደሮች ህገወጥ የመድኃኒት ስርጭትን ለመቆጣጠር የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ ነው።

በአካባቢዎቹ ባለፉት ሦስት ወራት በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ህገወጥ የመድኃኒት ንግድና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደደረሰ መረጋገጡን ጠቅሰዋል።

ጥናቱን ተከትሉ በደቡብ የኢትዮጵያ ክፍል ሁለት ከተሞች በተደረገ ድንገተኛ አሰሳም ከ24 የመድኃኒት መደብሮች ውስጥ በ17ቱ ከ3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ህገ ወጥ የመድሀኒት ክምችት መገኝቱን ጠቅሰዋል።

በተለይ በባለስልጣኑ ያልተመዘገቡ፣ የደህንነት ደረጃቸውን ጠብቀው ያልተከማቹ፣ የግዥና መሰል መረጃ የሌላቸው እንዲሁም በመንግስት የጤና ተቋማት ላይ ብቻ መገኝት ያለባቸው መድሀኒቶች በግል መደብሮች ሲሸጡ መገኘቱን አስረድተዋል።

ይህም በደቡብ የኢትዮጵያ ክፍል ህገወጥ የመድሃኒት ስርጭትና የኮንትሮባንድ ንግድ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን እንደሚያመላክት ገልጸዋል።

አቶ ፍቃዱ እንዳሉት ጽህፈት ቤቱ ህገ ወጥ መድኃኒት አከማችተው በተገኙ ጀምላ የመድኃኒት አከፋፋዮችና የመድኃኒት መደብር ባለቤቶች ላይ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ ወስዷል።

ባለድርሻ አካላት በተለይ የጤናውና የንግድ ዘርፍ አመራሮችና ባለሙያዎች ህገወጥ የመድሃኒት ንግድ በህዝብ ጤና ላይ የሚያደርሰውን ኪሳራ ተገንዝበው ስርጭቱን ለማስቆም የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዙ አስገንዝበዋል።  

ህብረተሰቡም ህገ ወጥ የመድኃኒት ንግድና ዝውውር ሲያጋጥመው ለሚመለከተው አካል እንዲያሳውቅና መድኃኒትም ሲገዛ ከህጋዊ ተቋማት ብቻ በማዘዥ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከ460 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የኮንትሮባንድ እቃዎችን መያዙን የገለጹት ደግሞ በጉምሩክ ኮሚሽን የሐዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ታደሰ ሜሪድ ናቸው።

ከተያዙት ውስጥ የኤሌክትሮንክስ እቃዎች፣ አልባሳትና መድሀኒት ቀዳሚውን ደረጃ መያዛቸውን አስረድተዋል።

"ቁጥጥሩ ቢጠናከርም ፍሰቱን ማስቆም አልተቻለም" ያሉት ሃላፊው፣ በተለይ ህገወጥ የመድኃኒት ዝውውርን ለመግታት ከኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

የደቡብ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ማሄ ቦዳ በበኩላቸው ህገ ወጥ የመድሐኒት ንግድ በሰው ጤና ላይ ከሚያደርሰው የከፋ አደጋ ባሻገር አሁን ላይ ህጋዊ የንግድ ሥርዓቱንም እያወከ መሆኑን ገልጸዋል።

ቢሮው ህገወጥ የመድኃኒት ስርጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን በየደረጃው ለሚገኝ ባለሙያና አመራር ከማስገንዘብ ባለፈ ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በመቀናጀት ለመከላከል እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ህብረተሰቡም ህገ ወጥ የመድሃኒት ንግድ ጉዳቱ ዘርፈ ብዙ በመሆኑ መረጃ በመስጠት ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ማገዝ እንዳለበት አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም