በዞኑ የወባ ወረርሽኝ እንዳይከሰት የቅድመ መከላከል ሥራ በቅንጅት እየተሰራ ነው -- ጽህፈት ቤቱ

136

ግምቢ፣ ነሐሴ 12/2014 (ኢዜአ) በምዕራብ ወለጋ ዞን የወባ በሽታ በወረርሽኝ መልክ እንዳይከሰት የቅድመ መከላከል ሥራ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ጤና ጽህፈት ቤት ገለጸ።

በዞኑ ጤና ጽህፈት ቤት የወባ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ቡድን መሪ አቶ ዲሪባ ጉተታ ለኢዜአ እንደገለፁት በዞኑ ካሉ 23 ወረዳዎች መካከል ስድስቱ ለወባ በሽታ ተጋላጭ ናቸው፡፡

በወረዳዎቹ በሽታው ክረምቱን ተከትሎ በወረርሽኝ መልክ እንዳይከሰት አስቀድሞ ለመከላከል ሕዝቡ፣ ባለድርሻ አካላትና ጽህፈት ቤቱ ተቀናጅተው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እስካሁን ባለው የመከላከል ሥራ በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ በሆኑ በአራት ወረዳዎች 36ሺህ 747 መኖርያ ቤቶች ላይ የኬሚካል ርጭት መካሄዱን ገልጸዋል።

አቶ ድሪባ 143 ሺህ 385 የወባ ትንኝ መከላከያ የአልጋ አጎበር ለነዋሪው መከፋፈሉን ገልጸው ህብረታሰቡ የአልጋ አጎበር በአግባቡ መጠቀም እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

በሁኑ ወቅት ተጨማሪ የአልጋ አጎበር ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡

ከክረምቱ ዝናብ ጋር ተያይዞ በሁሉም ወረዳዎች ለወባ ትንኝ መራባት መቹ የሚሆኑ ረግረጋማና ውሃ የሚያቁሩ ቦታዎችን በሕዝብ ተሳትፎ የመድፈን ተግባር እየተከናወነ ነው ብለዋል።

የግምቢ ወረዳ ነዋሪ አቶ ኢተፋ አምሳሉ በሰጡት አስተያየት አካባቢያቸው በአግባቡ በማጽዳትና ውሃ ያቆሩ አካባቢዎችን በመድፈን ከወባ በሽታ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን እየተከላከሉ መሆኑን ተናግረዋል።

ከጤና ባለሙያዎች ባገኙት ግንዛቤ መሰረት የአልጋ አጎበርን በአግባቡ በመጠቀም የወባ በሽታን  እየተከላከሉ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ሌላው የግምቢ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ቦንቱ ከሚሶ በበኩላቸው የወባ በሽታ መከላከያ የአልጋ አጎበር በአግባቡ ከመጠቀም ባለፈ ለወባ መራቢያ የሚሆኑ ቦታዎችን በአግባቡ በማጽዳት ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ከበሽታው መከላከል መቻላቸውን ተናግረዋል።

ሁሉም አካባቢውንና ለወባ ወረርሽኝ አመቺ የሆኑ ቦታዎችን በማፅዳት እንደርሳቸው ቤተሰቡንና ራሱን ከወባ ወረርሽን መጠበቅ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም