በአዲስ አበባና በዙሪያዋ ከተከሰተው ግጭት ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ፖሊስ አስታወቀ

80
አዲስ አበባ መስከረም 7/2011 በአዲስ አበባና በዙሪያዋ የተከሰተው ግጭት ለወጣቶች ገንዘብ በመስጠት ችግሩ እንዲባባስ ያደረጉ ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የፌደራል ፖሊስ አስታወቀ። የብሔር  ግጭት የሚመስል ነገር በመፍጠር በአገሪቱ ሰፊ ያለመረጋጋት ለመፍጠርና የተጀመረውን ለውጥ ለማደናቀፍ የተንቀሳቀሱ ቡድኖች በህግ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን የተናገሩት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል ዘይኑ ጀማል ናቸው። በተፈጠረው አለመረጋጋት ሳቢያም የሰው ህይወት ጠፍቷል፤ ንብረትም ወድሟል፤እንዲያም ሆኖ በአሁኑ ወቅት አካባቢዎቹ መረጋጋታቸውን ኮሚሽነሩ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ጠቁመዋል። ከግጭቱ ጋር በተያያዘ ዘረፋ መፈፀሙን የጠቆሙት ኮሚሽነር ጄነራሉ ፖሊስ የተዘረፈውን ከፍተኛ ንብረት የማሰባሰብ ስራ በማከናወን ላይ መሆኑን ገልፀዋል። ቡራዩና አካባቢዋ ላይ የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ በአዲስ አበባና አርባ ምንጭ ሰላማዊ ሰልፍ መካሄዱን ጠቅሰው ህዝቡ በሰልፉ ላይ ሀሳቡን ገልጾ ሲመለስ የተወሰኑ ቡድኖች ህብረተሰቡን ለማሸበርና ችግሩ ይበልጥ እንዲባባስ ጥረት ማድረጋቸውን ተናግረዋል። እነዚህ ቡድኖች ቦንብ ጭምር ይዘው እንደነበርና የጦር መሳሪያን ከፖሊስ ላይ መንጠቃቸውን ገልፀዋል። በዚህ ወቅት በተወሰደ እርምጃም  የአምስት ሰዎች ህይወት አልፏል፤ ሌሎች ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት  ደርሷል ብለዋል። በተለይ በአዲስ አበባ መርካቶና ፒያሳ አካባቢ ዘራፊዎች ለዝርፊያ ሲሰማሩ ፖሊስ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል። የብሔር ግጭት ለማስመስል የተሰራውን ስራ ህብረተሰቡ እንዲያውቀው ያሳሰቡት ኮሚሽነር ዘይኑ ህዝቡ ከለውጡና ከጽጥታው ሃይል ጎን እንዲቆም ጠይቀዋል። ወጣቱና ህዝቡም በእነዚህ እኩይ ተግባር ባለቸው ሃይሎች እንዳይታለል ኮሚሽነሩ አስገንዝበዋል። ፖሊስ ከዚህ በኋላ ከሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ጋር በመተባባር ችግር ፈጣሪዎችን የመለየት ስራ ይሰራል ሲሉም ተናገረዋል። "የፀጥታ ኃይሉ፤ ወደ ዲሞክራሲ የሚደረግ ሽግግር ለረጅም ጊዜ ታፍኖ ለነበረው ህዝብ የሚያጋጥም በመሆኑ ችግሮችን በትእግስትና በሆደ ሰፊነት ሊስተናግዱ ይገባል የሚል  አቋም ነበረው፤ ይህ ማለት ግን ጉልበተኛ ደካማው ያፈራውን ንብረት ይውሰድ፣ የጸጥታ ሃይሉን መሳሪያ ይቀማ ማለት ስላልሆነ ቀዩ መስመር የቱጋ ነው ብሎ አስምሮ መሄድ ያስፈልጋል" ብለዋል። ስለዚህ ቀዩን መስመር ለሚያልፈው ጉልበተኛና ወጣትን በማይወክሉት ላይ መንግስት የማያዳግም እርምጃ እየወሰደ ይሄዳል ነው ያሉት። ፖሊስ የመጀመሪያ ስራው ችግር ፈጣሪዎችን ለህግ ማቅረብ ሲሆን ከህግ በላይ የሆኑትን ግን ህግ ለማስከበርና እርምጃ ለመውሰድ ይገደዳል ሲሉም ኮሚሽነር ጄነራል ዘይኑ ጀማል አስጠንቅቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም