የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት ለድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጣና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀቱን አስታወቀ

160

ነሐሴ 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት በድሬዳዋ ለተመሰረተው ነጻ የንግድ ቀጣና ቀልጣፋና ፈጣን የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀቱን አስታወቀ።

በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተመርቆ ስራ የጀመረው የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጣና ለወደብ ካለው ቅርበት አኳያ ምጣኔ ሃብቱ ላይ የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑ ተነግሯል።

የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጣና የንግድ ሰንሰለቱን በማቀላጠፍ የኢትዮጵያን አምራችነት ይበልጥ የሚያጠናክርና  የኢትዮጵያን መጻኢ ብልጽግና እውን ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑንም መግለፃቸው ይታወሳል።

ድሬዳዋ ከጂቡቲ በቅርብ ርቀት የምትገኝ ከመሆኗ ባሻገር የኢትዮ-ጂቡቲ የባቡር ትራንስፖርት መስመር የሚያልፍባት መሆኗ ለሎጂስቲክስ አገልግሎት ምቹ ያደርጋታል።

የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ሃላፊ ዶክተር አብዲ ዘነበ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት፤ የባቡር ትራንስፖርት በድሬዳዋ ለተመሰረተው ነጻ የንግድ ቀጠና ያለውን ጠቀሜታ አብራርተዋል።

ወደ ነፃ የንግድ ቀጠናው ለሚገቡ አምራቾች ወጪና ገቢ ዕቃዎችን ቀልጣፋ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

የድሬዳዋ ደረቅ ወደብ ከባቡሩ ጋር ባለው ትስስር ገቢና ወጪ እቃዎችን ማውረድና መጫን የሚችል በመሆኑ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችል ነው ያስረዱት።

ድሬዳዋ በተዘረጉ የባቡርና መንገድ መሠረተ ልማቶች፣ ኢንዱስትሪ ፓርክና የደረቅ ወደብ ነፃ የንግድ ቀጣናውን ዕውን ለማድረግ አመቺ እንደሚያደርጋትም ተናግረዋል።

ባለሃብቶች በፍጥነትና በጥራት ገቢና ወጪ እቃን የማጓጓዝ አገልግሎት በማግኘት በነጻ የንግድ ቀጠናው ያለውን እድል መጠቀም እንደሚችሉም ጠቁመዋል።  

በኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ላይ የታለመለትን ግብ እንዲያሳካ በባቡር ጭነት አገልግሎት በኩል የተጠናከረ ስራ እየተከናወነ ሲሆን ለዚህም የድሬዳዋ ባቡር ጣቢያን በሙሉ አቅሙ ለማንቀሳቀስ እየተሰራ መሆኑን ጨምረዋል።

ነፃ የንግድ ቀጣናዎች የልዩ ኢኮኖሚ ቀጣናዎች አካል ሲሆኑ፣ በውስጣቸው እሴት የሚጨምሩ የሎጂስቲክስ አገልግሎቶች፣ የማምረት ሥራዎችና ንግድ እንቅስቃሴ የሚከናወንባቸው እንደሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም