የሚያለያዩ ችግሮችን እየነቀልን፤ ችግኞችን እንተክላለን- ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ

293

ነሐሴ 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) የሚያለያዩ ችግሮችን እየነቀልን፤ ችግኞችን እንተክላለን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

በአዲስ አበባ በአንድ ጀምበር የ4 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው።ከንቲባዋ በንፋስ ሰልክ ላፍቶ ሀጫሉ ሁንዴሳ መንገድ ላይ አሻራቸውን አኑረዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ የኢፌድሪ መከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይን ጨምሮ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ከተማ በአንድ ጀንበር የ4 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል፡፡

በወቅቱ ከንቲባዋ በአዲስ አበባ ከተማ 7.5 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ ከእጥፍ በላይ ማሳካት አለብን በማለት ተነስተን 15.5 ሚሊየን ችግኝ በመትከል ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ መላውን የከተማችን ነዋሪ በእጅጉ እናመሰግናለን ብለዋል፡፡

ችግኞቹ እየተተከሉ ያሉት አስፈላጊና ጠቃሚ በሆኑ ቦታዎች ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች፤ በአዲስ አበባ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እየተከሰተ ያለውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል በሚያግዝ መልኩ እየተተከለ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ዛሬ ያበቃነው የክረምቱን ዘመቻ ነው እንጂ ከተማችንን አረንጓዴ ማድረጋችን ይቀጥላል ያሉት ከንቲባ አዳነች፤ አደባባዮችን እናስውባለን ውበትና ጥላ የሆኑ ዛፎችን በመትከል ከተማችንን ፅዱና ረንጓዴ ማድረጋችንን እንቀጥላለን ሲሉም ገልፀዋል፡፡

በዚሁ ንግግራቸው ከንቲባ አዳነች የሚያለያዩ ችግሮችን እየነቀልን ችግኞችን እየተከልን አብሮነትን እያጠናከርን እንቀጥላለን ማለታቸውን የከንቲባ ጽህፈት ቤት መረጃ አመልክቷል።