ወለጋ ዩኒቨርሲቲ በሦርጋ ሐይቅ አካባቢ የአረንጓዴ ቱሪዝምና ዕፅዋት ፓርክ ለመገንባት ቦታ ተረከበ

257

ነቀምቴ ነሐሴ ፤ 11/2014 (ኢዜአ)፡- ወለጋ ዩኒቨርሲቲ በምሥራቅ ወለጋ ዞን ነቀምቴ ከተማ አከባቢ የሚገኘውን ሦርጋ ሐይቅ አካባቢ የአረንጓዴ ቱሪዝምና ዕፅዋት ፓርክ ለመገንባት ቦታ ተረከበ።

ከነቀምቴ ከተማ አስተዳደር ጋር  በተካሄደው የርክክብ ሥነ-ሥርዓት ወቅት የዩኒቨርሲቲው የሥነ ሕይወት መምህርና የተፈጥሮ ሳይንስ ዲን ዶክተር ሞሲሳ ገለታ ፤ ሐይቁ  አረንጓዴነቱ ተጠብቆ የቱሪዝም አገልግሎት እንዲሰጥ ለማስቻል ቦታውን መረከባቸውን ተናግረዋል፡፡

ወለጋ ዩኒቨርሲቲ በሐይቁ አካባቢ የወለጋን ሕዝብ ባህልና እሴት የሚያንጸባርቅ ሆቴልና ሎጆች ላይ ትኩረት ያደረጉ ግንባታዎችን እንደሚያካሄድ አስታውቀዋል።

የቱሪዝምና ዕፅዋት ፓርኩ በሆቴልና ቱሪዝም የትምህርት መስክ ተማሪዎችን በተግባር በማስደገፍ ለማስተማር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ገልጸዋል፡፡

በባህላዊ መንገድ ከሐይቁ ዓሣ  ሲመረት መቆየቱን የጠቆሙትዶክተር ሞሲሳ፣ “በጥናትና ምርምር የተደገፈ ዓሳ በጥራትና በብዛት በማምረት የአካባቢው ሕዝብ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ ይሰራል” ብለዋል ፡፡

ሐይቁን ማልማት በሥራ አጥ ቅነሣ ውስጥ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጠቁመው፤  ጀልባዎችን በማስገባት የመዝናኛ ስፍራ ለማድረግ መታቀዱን ተናግረዋል።

ቦታውን የእፅዋት እና የእንስሳት የአትክልት ሥፍራ / botanical and zological garden/ በማድረግ የተለያዩ ዕፅዋትና የዱር እንስሳት ላይ የጥናትና ምርምር ሥራ በማካሄድ የትምህርትና የምርምር ማዕከል እንደሚደረግም አስረድተዋል፡፡

የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሀሰን ዩሱፍ በበኩላቸው፤ ሐይቁ የሚገኝበት አካባቢ ለዓይን የሚማርኩ የተፈጥሮ ደኖች በመኖራቸው ተቋሙ ይህንን ትልቅ ሀብት  በመረከብና በማልማት የቱሪዝም መስዕብ ቦታ በማድረግ የመዝናኛ ቦታ ይደረጋል ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡

በተፈጥሮ ደኑና በውስጡ በሚገኙ የዱር እንስሳት ላይ ጉዳት ሳይደርስ እሴት በመጨመር በዕውቀትና በሙያ ተደግፎ  በማልማት ለመማር ማስተማሩ፤ ለጥናትና ምርምር ሥራዎች  ለማመቻቸት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

የምሥራቅ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወጋሪ ነገራ ፤ ዩኒቨርሲቲው በሐይቁ ላይ የቱሪዝምና ዕፅዋት ፓርክ ለመገንባት መዘጋጀቱ የአካባቢውን የተፈጥሮ ሀብት በመጠበቅ  አረንጓነቱን ሳይለቅ እንዲቆይ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።

ሥራ አጥ ወገኖች በማህበር ተደራጅተው   በመሰማራት የማህበራዊና የኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸውን ለማቃለል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ነው ያመለከቱት።

የነቀምቴ ከተማ ነዋሪ አቶ ናስር ኑሩ በሰጡት አስተያየት፤ ሰው ሠራሹ የሦርጋ ሐይቅ ከተገነባ ዘመናትን  ቢያስቆጥርም ለነቀምቴና አካባቢዋ ነዋሪዎች የሰጠው ጥቅም አለመኖሩን ገልጸዋል።

የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ቦታውን በመረከብ በሳይንሳዊ መንገድ የጥናትና ምርምር ማዕከል በማድረግ ሕዝቡ ከሐይቁ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩ ተስፋ ሰጪ መሆኑንም ተናግረዋል።

ሦርጋ ሐይቅ ውሃ የተኛበት 15 ሄክታርና የአካባቢው መሬት ስፋት ደግሞ 30 ሄክታር መሆኑን ዩኒቨርሲቲን በመረጃ ምንጭነት ጠቅሶ የኢዜአ ሪፖርተር ከሥፍራው ዘግቧል፡፡