የልዩ ተሰጥኦ ባለቤት ለሆኑ ታዳጊ ወጣቶች ሳይበር ደህንነት ስልጠና እየተሰጠ ነው

373

ነሐሴ 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) የልዩ ተሰጥኦ ባለቤት ለሆኑ ታዳጊ ወጣቶች ሳይበር ደህንነት ስልጠና እየተሰጠ ነው።

በስልጠናው ላይ ከተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች የተውጣጡ 60 ታዳጊዎች የተሳተፉ ሲሆን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አገልግሎት ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የሚሰጥ ስልጠና መሆኑ ታውቋል።

በመርሃ ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ የተገኙት የስራና  ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል፤ የሳይበር ደህንነትንና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በማስጠበቅ ሒደት በቴክኖሎጂ የበቁ ወጣቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

የወጣቶችን ልዩ ተሰጥኦ በማዳበር በዲጂታሉ ዓለም ሀገራቸውን ማሳደግ የሚችሉ ስልጠናው ትርጉም ያለው መሆኑንም ተናግረዋል።

በዲጂታሉ መስክ ለወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውን ጠቁመው ዘርፉን ይበልጥ ለማጠናከር  የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ባይሳ በዳዳ በበኩላቸው ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚመረቁ ተማሪዎችም የሳይንስና ቴክኖሎጂ እውቀት እንዲገበዩ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ ውስጥም ፈጠራን በማበረታታትና ድጋፍ በማደረግ በቴክኖሎጂ እውቀት ብቁ የሆኑ ተመራቂዎችን ለማፍራት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

በመሆኑም ተቋማት በቅንጅት በመስራት ብቁና የፈጠራ ክህሎት ያለው ትውልድ ለማፍራት መስራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በ2025 ዓ.ም ለመድረስ ያስቀመጠችው የዲጂታላይዜሽንን ግብን ለማሳካትም በትኩረት እየተሰራ ስለመሆኑም አንስተዋል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ፤ ስልጠናውን እንዲሳተፉ የተመረጡት ወጣቶች አገልግሎቱ ያወጣውን መስፈርት አሟልተው የተገኙ ናቸው ብለዋል።

በየጊዜው በሀገር ላይ የሚቃጣ የሳይበር ጥቃትን ለመከላከል በቴክኖሎጂ ላይ እውቀት ያለው የሰው ሃይል ማፍራት አስፈላጊ እንደሆነም ተናግረዋል።

በመሆኑም በዘርፉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ብቁ የሆነ የሰው ሃይል ለማፍራት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ሳይበር ታለንት ማዕከል የሚበለጽጉ የተለያዩ የፈጠራ ስራዎችን የማስመዝገብ ስራ እየተከናወነ እንደሆነም ጠቁመዋል።

በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም የሳይበር ደህንነት ክበቦች እንዲጠናከሩ መደረጉን ገልጸዋል።

የስልጠናው ተሳታፊ ታዳጊ ወጣቶች በበኩላቸው በሳይበር ደህንነት ላይ አገራቸውን ለማገልገል ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።

በሳይበር ደሕንነት ዙሪያ የሚሰጣቸው ስልጠናም እራሳቸውን ለማብቃት እንደሚያግዛቸው አክለዋል።